የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሠራተኞች 11ኛውን የሲቪል ሰርቪስ ቀን አከበሩ

የዘንድሮ የሲቪል ሰርቪስ ቀን በስነ ምግባሩ የተመሰገነ ሲቪል ሰርቫንት ለኢትዮጵያ ህዳሴ!” በሚል መሪ መልዕክት በአገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዚሁ መነሻ ቀኑ በተለያዩ ዝግጅቶች ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ/ም በኢንስቲትዩቱ ዋና መ/ቤት ተከብሮ ውሏል፡፡

በዕለቱ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በዓሉን የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ እንደተናገሩት ሲቪል ሰርቫንቱ የሕዝብ አገልጋይ መሆኑንና አገራችን አሁን ለደረሰችበት ዕድገት የሲቪል ሰርቫንቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም አገልግሎቶቹ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ፣ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማድግ የግንባር ቀደም መሪነት ሚናን መጫወት እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ 

ሲቪል ሰርቪሱ መልካም አስተዳደርን በማስፈንየኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ የላቀ ድርሻው ያለው መሆኑን በመጠቆም፤ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ሲገልፁ ሲቪል ሰርቫንቱ የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ የሚሰጠውን አገልግሎት ታስቦ መዋል ስላለበት የቀኑ መከበር ትክክለኛ እና አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

በበዓሉ ላይ በሥነ ምግባር መርሆች ዙሪያ መነሻ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን የፓናል ውይይት ተደርጎበት በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡ 

 

በሌላ በኩል በዚሁ በዓል ላይ ኢንስቲትዩት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ምርታማነትን እና ጥራትን የሚጨምሩ ተመራጭ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ እንዲሁም የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ  በማፍለቅ፣ በማላመድ፣ በማስተዋወቅና ፍላጎትን በመፍጠር እየሰራ የሚገኝ ተቋም ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን የተለያዩ ለአገሪቷ ግብርና ዕድገት የሚያግዙ የምርምር መጽሐፎችም በኢንስቲትዩቱ ታትመው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ በዚሁ መሠረት  “Retrospects and Prospects of Ethiopian Agricultural Research” የተሰኘ በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪዎች በዶ/ር ፈንታሁን መንግስቱ፣ በአቶ አበበ ቅሩብ እና  በአቶ ፍስሐ ዘገዬ የተፃፈ መጽሐፍ በዚሁ ቀን ተመርቋል፡፡