ኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢስቲትዩት በ2009 በጀት ዓመት የቴክኖሎጂና መረጃ አቅርቦትን አስመልከቶ ከተለያዩ ሚድያዎች ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡ 

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2009 በጀት ዓመት የቴክኖሎጂና መረጃ አቅርቦትን አስመልከቶ  ከተለያዩ ሚድያዎች ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በጋዜጣዊ መክፈቻው የህዝብ ግንኙነትና አ/ን/ባ/ዳይሬክተር አቶ ፍስሐ ዘገየ እንደገለጹት የጋዜጣዊ መግለጫው ዋና ዓላማ በ2009 በጀት ዓመት ኢንስቲትዩቱ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በተፈትሮ ሀብት ጥበቃ ዘርፍ ተመራምሮ ያቀረባቸውን ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ፣ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ፣ እና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲሁም ለመላው ህብረተሰብ መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም ለማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ገለቲ  የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ ኃላፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በጋዜጣ መግለጫ ላይ ለተገኙ ከ20 በላይ ለሚሆኑ የሚዲያ አካላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ድሪባ ገለቲ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ ከተልፅኮው መነሻነት በሶስት ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ትኩረቱን በማድረግ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በዋናነት በሰብል፣ በእንሰሳት፣ በአፈርና ውሃ፣ በግብርና ሜካናይዜሽን እንዲሁም በግብርና ምጣኔ ሃብት ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን በማቅረብ ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ የማድረግ ተግባር በሰፊው የተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም  በምርምር የወጡትን ቴክኖሎጂዎች በተለያየ መንገድ ለተጠቃሚው ለማድረስ ኢንስቲትዩቱቴክኖሎጂዎቹን ማስተዋወቅና ፍላጎት መፍጠርን ሌላው የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ ፍላጎት የተፈጠረባቸውንና ተቀባይነት ያገኙትን ቴክኖሎጂዎች መነሻ የሚሆን ለቴክኖሎጂ አባዥ ተቋማት በማቅረብ እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በቀጥታ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢንስቲትዩቱ በድምሩ 586 ቴክኖሎጂና መረጃዎችን ለማቅረብ አቅዶ 564 /96%/ ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን ለማቅረብ ችሏል፡፡ ይህ ውጤት ከ2008 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ ብልጫ አለው /91 %/፡፡ ከሰብል ዝርያ አቅርቦት አኳያ ሲታይ በበጀት ዓመቱ ኢንስቲትዩቱ  48 የሰብል ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ የቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የለቀቃቸው 2 የቴምር ዝርያዎችና 2 የፓልማርዝ ዝርያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የቀረቡት ዝርያዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዝርያዎች ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚደርስ የምርት ልዩነት ያላቸው ሲሆን ድርቅ፣ ተባይ፣ በሽታንና ሌሎችም ችግሮችን የመቋቋም አቅም ያላቸው መሆናቸውን ተብራርቷል፡፡ በሌላ በኩል በበጀት አመቱ 51,217 ወንዶችና 17,949 ሴቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችን በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ቅድመ ማስፋፋት ስራዎች አንዲሳተፉ ማድረግ መቻሉን ገልፀው ለ39,567 የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ደግሞ በዚሁ ዙሪያ  የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተችሏል ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም በመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት በዓመቱ በሰብል ምርምር፣ በእንሰሳት ምርምር፣ በመሬትና ውሃ ሃብት ምርምር፣ በግብርና ሜካናይዜሽን ምርምርና በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር መስክ የቴክኖሊጂ ብዜት አቅርቦት ስራዎች በስፋት መሰራታቸው ተገልጻል፡፡

ዶ/ር እሸቱ ደርሶ፤ የተቋሙ ሰብል ምርምር ዳይሬክተር በበኩላቸው በዘርፉ በ2009 ዓ.ም በቴክኖሎጂና መረጃ አቅርቦት ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሰራ የቆየ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ ጎን ለጎንም በተጠቃሚዎች ግንዛቤ የማስጨበጥና ፍላጎት የመፍጠር፣ የቅድመ ማስፋፋት ስራዎችን እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የሰብል ምርምሮችን የማስተባበርና ድጋፍ የመስጠት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስተው የነበሩ የሰብል በሽታዎች፣ ነፍሳትና ተባይ ጥበቃና መከላከል ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም በበቆሎ፣ ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ዝንጅብል፣ ባቄላ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ሰሊጥና ኑግ ላይ የተከሰቱ በሽታዎችንና ተባዮችን መከላከልና መቆጣጠር ላይ በሰፊው ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ፣ በአፈር አሲዳማነትና ጨዋማነት፣ ምክንያት የሚፈጠሩ እነዚህና መሰል በሽታዎችን ለመከላከል ለመቆጣጠርም የምርምር አቅምን ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የምርት መጠን ልዩነትን፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን፣ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ የተከሰቱ በሽታዎችና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ዙሪያ፣ በግብርና ሜካናይዜሽንና ባዮቴክኖሎጂ እንዲሁም መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች ከተለያዩ ሚድያዎች በመጡ ጋዜጠኞች የተነሱ ሲሆን፣ በሚመለከታቸው የስራ ክፍል ኃላፊዎች ሰፋ ያለ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡