በግብርና ምርምር ውጤቶች ጥበቃ ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ፤

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሕዝብ ግንኙነትና የአእምሮአዊ ንብረት ባለቤትነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ለኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አካላት እና ከፍተኛ ተመራማሪዎች የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ እና የግብርና ኢኖቬሽን  ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰኔ 29 ቀን  2009 ዓ.ም. በዋናው መ/ቤት ተሰጠ፡፡

የሥልጠናውን ዓላማ የህዝብ ግንኙነትና የአእምሮአዊ ንብረት ባለቤትነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሐ ዘገዬ ለተሳታፊዎቹ በገለጹት መሰረት የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ተመራማሪዎች ስለ አእምሯአዊ ንብረት ጥበቃ ህጎች ምንነት፣ ጠቀሜታና አስገዳጅነት እንዲሁም በጀነቲክ ሃብት አጠቃቀም ላይ አጠቃላይ  በሕጉ ማዕቀፎች ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው፡፡ ይህንን መሰል ስልጠናዎችም በኢንስቲትዩቱ የምርምር ማዕከላት ለሚገኙ ተመራማሪዎች በቀጣይ የሚሰጥ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርታማነትንና ጥራትን የሚጨምሩ በምርምር ተሻሽለው የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ እና ከፊል አርብቶ አደሩ ማቅረብ የኢንስቲትዩቱ ዋና ተግባር ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው የምርምር ስራ እና የሚወጡ አዳዲስ  ቴክኖሎጂዎች የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ተመራማሪውም የፈጠራ ችሎታውን ለማሳደግ በዚህ ረገድ የማትጊያ ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ የገለፁት ስልጠናውን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ ናቸው፡፡

ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በግብርና ምርምሩ ዘርፍ የአእምሯዊ ንብረት የሚባሉትን የምርምር ውጤቶች ግኝት ደህንነት እና ባለቤትነት ማስጠበቅ የሚቻለው በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ የተማራማሪው ግንዛቤ በማስፋት እና ሕጉንም ተግባር ላይ በማዋል በመሆኑ እንዲዚህ አይነት ስልጠና አስፈላጊ እና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረው፤ ኢንስቲትዩቱም ከአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የቴክኒካል ክፍል ዳይሬክተሮች፣ ም/ዳይሬክተሮች እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል፡፡