በስርአተ ጾታ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የለውጥ አመራር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ለኢንስቲትዩቱ የድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች በስርአተ ጾታ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከሀምሌ 25-27 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋናው መ/ቤት ተሰጠ፡፡

የለውጥ አመራር ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ ለተሳታፊዎቹ በገለጹት መሰረት ሥልጠናው የኢንስቲትዩቱ ሴቶችና ተመራማሪዎች ስለስርአተ ጾታ ፓኬጅ ህጎች ምንነት፣ ጠቀሜታና አስገዳጅነት እንዲሁም ተጠቃሚነት ላይ አጠቃላይ  በሕጉ ማዕቀፎች ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡

ሴቶች እራሳቸውን በማብቃት ተወዳዳሪና የንብረት ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸው ብሎም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እናም በምርምርም የፈጠራ ችሎታቸውን ለማሳደግ በዚህ ረገድ የማበረታቻ ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ የገለፁት ስልጠናውን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዲሪባ ገለቲ ናቸው፡፡

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የስርአተ ጾታ ምርምር ዘርፍ ም/ ዳይሬክተር ዶ/ር ረሂማ ሙሰማ በበኩላቸው በዘር ያሉ መልካም አጋጣሚወች እና ተግዳሮቶችን ለስልጠናው ተሳታፊች ያመላከቱ ሲሆን የሴቶችን ደህንነት፤ ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት ማስጠበቅ የሚቻለው በስርአተ ጾታ ዙሪያ በጋራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት እና በሕግ ማዕቀፎቹ ዙሪያ የሴቶችን ግንዛቤ በማስፋት አንዲሁም ሕጉን ተግባር ላይ በማዋል በመሆኑ እንደዚህ አይነት ስልጠና አስፈላጊ እና ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ሀገር በሴቶች ላይ የተሻሉ እይታዎችና ግንዛቤዎች እየተፈጠሩ ያሉ ቢሆንም አሁንም ግን በጋራ መስራት ያለባቸው ብዙ ተግባራት እንዳሉ ብሎም ኢንስቲትዩቱ እስከ ማዕከል ድርስ ወርዶ የሴቶች ፎረም ማቋቋም እንደሚገባው ልብ ሊባል የሚገባው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከማዕከል እና ከዋናው መስሪያ ቤት የተውጣጡ የቴክኒካል ክፍል ሰራተኞች፣ተመራማረወች  እና ከሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር የመጡ ባለሙያዎች  ተሳትፈዋል፡፡