ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አገር አቀፍ የተጓዥ መስክ ቀን አካሄደ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአገሪቱን ሥነምህዳር በመከተል በስሩ በሚገኙ የፌደራል የምርምር ማዕከላትን በማስተባበር እና ከሌሎች የምርምርና ልማት አጋር ኣካላት ጋር በመቀናጀት በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ዋና ዋና የምርምር መስኮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ፣ለአግሮ-ኢንደስትሪ እና ለወጪ ንግድ ግብዓት የሚሆኑ አማራጭ ቴክሎጂዎችን የማላማድ፣ የማስተዋወቅና የማስፋት የሥራዎችን ለማስጎብኘትና ለመገምገም አገር አቀፍ የተጓዥ መስክ ቀን አካሄደ፡፡

የተጓዥ መስክ ቀኑ ዋና ዓለማ የ2009/10 መኸር ወቅትን ተከትሎ በተመረጡ የምርምር ማዕከላት የተከናወኑትን የምርምር ሙከራ እና በአርሶ አደር ደረጃ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ተግባራትን በማስጎበኘት ግንዛቤ ለመፍጠርና በጋራ ለመወያየት ነው፡፡

የተጓዥ መስክ ቀኑ በደ/ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል የጤፍና የመኮሮኒ ስንዴ ቴክኖሎጂዎችን በመጎበኘት ተጀምሮ ባኮ ብ/በቆሎ ምርምር ማዕከል የበቆሎ ቴክኖሎጂ፣ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በገብስ ፣በሽንብራ እና በባቄላ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሰራውን ስራ ፣ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በቆላ ፍራፍሬ ላይ የተከናወኑ የምርምር ሥራዎችን እና ቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በባቄላ እና በስንዴ ቴክኖሎጂ ላይ የተከናወኑትን ሥራዎች በመጎበኘት እና የማጠቃለያ ውይይት በማድረግ ተጠናቋል፡፡

በተካሄደው የተጓዥ መስክ ቀን ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግብርና ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ/አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች ፣ የሚዲያ አካላት እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡