የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል የመነሻ ዘር የማስፋፋት እና ማባዛት ሥራ እየሠራ ነው

የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያወጣቸውን የተሻሻሉ የሽንብራና ምስር ቴክኖሎጂዎችን በምስራቅ ሸዋ ዞን  በአድአ ወረዳና አካባቢው ካሉ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ማህበራት ጋር በመሆን ያከናወናቸውን የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎች ለአካባቢው አርሶ አደሮች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ፕሮጀክት አስተባባሪዎች፣ ከተለያዩ ክልል የመጡ የግብርና ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ለሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ህዳር 12 ቀን 2010 ዓ.ም አስጎብኝቷል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል USAID-ICARDA ICRISAT/TL-III KAFACI project እና  OSE- BENEFIT-ISSD ፕሮጀክቶች ጋር በመተባበር የሽንብራና ምስር ቴክኖሎጂዎች ማሻሻያ ምርምር  እንዲሁም የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ማዕከሉ እነዚህን የምርምር ተግባራት ለማከናወን አቅዶ ወደ ስራ የገባው በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያጋጠሙ ያሉ የምርት እጥረቶችንና በተመሳሳይም የሰብል ምርት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታትን አላማው አድርጎ ነው፡፡

ማዕከሉ በአድአና አካባበቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን በክላስተር በመደራጀት የሚያከናውኑትን የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎች በመደገፍ፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ የአፈር አያያዝና ውሃ አጠቃቀም፣ የማሳ ዝግጅት፣ የሰብል እንክብካቤ እንዲሁም ድህረ ምርት ሂደትን የተመለከቱ ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ጥራቱን የጠበቀና ምርታማ ሰብል በማምረት እራሳቸውንና አካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ከማድረግ አልፈው በአገር አቀፍ ደረጃ የመነሻ ዘር ስርጭት እጥረትን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

 

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በሰብል እና በእንስሳት ምርምር ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ በማቅረብ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሰብል ቅድመ መስራች ዘር የማባዛት ተግባር የሚያከናውን አንጋፋ ማዕከል ሲሆን፤ በጥራጥሬ የሽንብራና ምስር ምርምር ብሔራዊ አስተባባሪ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡