የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለያዩ የሰብል ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና የማስፋፋት ሥራ እየሠራ ነው

 

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያወጣውን የተሻሻለና የተሞከረ   የማሽላ ቴክኖሎጂ እና ከተባባሪ ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን እያላመደ የሚገኘውን የስንዴ ቴክኖሎጂ በተመለከተ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባንባሲ እና በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ህዳር 16-17 ቀን 2010 ዓ/ም የመስክ ጉብኝት አካሄደ፡፡ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የክልሉን የግብርና ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉና ተጠቃሚውን ማህበረሰብ መሰረት ያደረገ የተለያዩ የምርምር ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣትና ውጤታማ የሆኑ የአሰራር ስልቶችንና መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የክልሉን እምቅ አቅም ይበልጥ ለመጠቀም የሚረዳ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ በትጋት በመስራት ላይ የሚገኝ ማዕከል ነው፡፡   

 

ማዕከሉ ባካሄደው  የመስክቀንበዓል ላይ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ግዲሳ እንደተናገሩት ክልሉ ለግብርና ምቹ ስነ ምህዳር አላቸው ከሚባሉት ክልል አንዱ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ የማምረት ችሎታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ይህ እምቅ ኃይል በምርምር የወጡ ቴክኖሎጂዎች መታገዙ አገሪቷ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ለምትገኘው ውጤት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ማዕከሉ የአካባቢው ተጠቃሚ ማህበረሰቦች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲያድግ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችና ሙከራዎች እያደረሰ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ በዚሁ መስክ ቀን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ባንባሲ ወረዳ በአርሶ አደር ማሣ ላይ ለጉብኝት የበቃው ከምርምር ማዕከሉ በምርምር የተገኘው  ‹‹አሶሳ 1›› የተሰኘው የተሻሻለ የማሽላ ቴክኖሎጂ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

 

ዳይሬክተሩ አክለውም የምርምር ማዕከሉ ከማሽላ ቴክኖሎጂ ጎን ለጎንም በአካባቢው ላይ የተለያዩ የሰብል ቴክኖሎጂዎችን ከተባባሪ ማዕከላት ጋር በመቀናጀት የምርምር አድማሱን ለማስፋት የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ቴክኖሎጂ በማላመድ ለአርሶ አደር ለማዳረስ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረው ከዚህ መካከል ስንዴና ሩዝ በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ባንባሲ ወረዳ መንደር 47 ነዋሪ አርሶ አደር ቀሲስ ወዳጅ ታረቀኝ ቀደም ሲል የአካባቢ ማሽላ ዝርያ በመጠቀም የልፋታቸውን ዋጋ እንደማያገኙና የሚገኘው ምርትም በኑሮአቸው ላይ ለውጥ ያላመጣ መሆኑንና የሚገኘው ምርትም በሄክታር 6-8 ኩንታል ብቻ መሆኑን አውስተው የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ባደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍ እና ‹‹አሶሳ 1›› የተሰኘውን አሻሽሎ ያወጣውን የማሽላ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናቸው በሄክታር ከ40-45 ኩንታል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ማዕከሉ የአካባቢውን አርሶ አደሮች በሌሎች ሰብሎች ተጠቃሚ ለማድረግ  ከቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር የተገኘውን ‹‹ደንደአ›› የተሰኘ የስንዴ ቴክኖሎጂ በማላመድ እና በኩታ ገጠም ለተደራጁ  አርሶ አደሮች በማዳረስ የማላመድ ስራ እየሰራ ሲሆን  የተደራጁት አርሶ አደሮችም በተደረገላቸው ድጋፍና ያዩት የስንዴ ቡቃያ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ስራ መሆኑን በዕለቱ መስክ ቀን  ጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት አርሶ አደሮች ገልፀዋል፡፡ 

 

በመስክ ቀኑ  በአርሶ አደር ማሳ ላይ እየተባዛ ያለው የማሽላ ቴክኖሎጂ፣ በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮች እያላመዱ የሚገኙት  የስንዴ  ማሳ እና በማዕከሉ ምርምር ጣቢያ ውስጥ እየተሞከረ ያለውን የሩዝ ማሳ እና የቡና ተክል እንዲሁም አጠቃላይ የማዕከሉን እንቅስቃሴ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽ/ቤት ሃላፊ፣ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ተጎብኝቷል፡፡