የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ሠራተኞችና አመራሮች የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እና የዓለም የኤች.አይ.ቪ.ኤድስ ቀንን በጥምረት አከበሩ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ሠራተኞች ‹‹በሕገ-መንግስታችን የደመቀ ሕብረ-ብሔራዊነታችን ለሕዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ በአገራችን የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንና በዓለም ለ30ኛ ጊዜ በአገራችን ለ22ኛ ጊዜ ‹‹አሁንም ትኩረት ለኤች/አይ/ቪ ኤድስ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የዓለም የኤች/አይ/ቪ ኤድስ ቀን ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በማጣመር በዋናው መ/ቤት በህሩይ አዳራሽ በድምቀት አከበሩ፡፡ 

በዚሁ መሠረት የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኢንስቲትዩቱ ሲከበር አቶ ፍስሐ ዘገየ የሕዝብ ግንኙነትና አ/ን/ባ/ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደተናገሩት የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የጸደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው ሶስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በወሰነው መሰረት በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንደሚከበር እና ዋና ዓላማውም የሀገራችን ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ላፀደቁት ህገመንግስት ያላቸውን ክብርና ታማኝነት ለመግለጽና ያስገኘላቸውን መብቶች፣ ጥቅሞች እና ድሎች በመዘከር ለቀጣይ የልማት ስራዎች መነቃቃት እንዲሁም ተነሳሽነትን ለመፍጠር ነው፡፡

ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ የኢንስቲትዩቱ የም/ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ዝግጅቱን በከፈቱበት ወቅት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በአል ሲከበር በህገ መንግስቱ  አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ራእይን እውን እንዲሆን መሆኑን እና ከዚሁ ጎን ለጎን በኢንስቲትዩቱ በመከበር ላይ ስለሚገኘው የአለም የኤች አይ ቪ ኤድስ የወቅቱ ስርጭት ምን እንደሚመስል እና የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸውና በስፋት መሰራት እንዳለበት ግንዛቤ አስጨብጠዋል፡፡ አቶ ፍስሀ ዘገዬ በበኩላቸው የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ያወጣውን መረጃ መነሻ አድርገው በአገሪቱ በ2009 ዓ/ም 718 ሺህ 550 ዜጎች ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ እና እ/ኤ/አ በ2010 ብቻ 70000 ኢትዮጵያዊያን በኤች አይ ቪ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ለተሳታፊዎች አብራርተው ገልጸዋል። 

የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች በዕለቱ በዓሉን አስመልክቶ ጥያቄና መልስ ውድድር፣ ሥነ ግጥም እና የውይይት መነሻ ፅሑፍ በማቅረብና ሰፊ ውይይት በማድረግ ዕለቱን አክብረዋል፡፡