አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማንደፍሮ ከኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት ጋር ውይይት አደረጉ

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ከየካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ዶ/ር ችሎት ይርጋ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአስተዳደርና አቅም ግንባታ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡  

ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ ዛሬ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን የትውውቅና የሥራ ክፍሎቹ የሚተገብሯቸውን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከማኔጅመንት አባላቱ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም የቴክኒክ፣ የቴክኒክ ድጋፍና የአስተዳደር ሥራ ክፍሎች በበጀት ዓመቱ በማከናወን ላይ የሚገኙትን ሥራዎች አስመልክቶ አጭር ገለጻ አድርገዋል፡፡

የሥራ ክፍሎቹን ገለጻ መሰረት በማድረግም ተጨማሪ ማብራርያ እና በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተው አስረድተዋል፡፡ በማከልም እንደ ሁኔታው በተለይ ከእያንዳንዱ የሥራ ክፍሎች ጋር ሰፊና ጠለቅ ያለ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ድጋፍ የሚደረግባቸውን ጉዳዮች እንደሚለዩ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ማንደፍሮ በመጨረሻም የጊዜ አጠቃቀም፣ የሚተገበሩ የምርምር ፕሮግራሞች፣ የተመራማሪ ሰው ኋይል፣ ውጤታማ የበጀት አጠቃቀም ዙሪያ መከናወን ያለባቸውን ሥራዎች የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኢንስቲዩቱ ያለበትን ጥንካሬ መሰረት በማድረግ ለላቀ ውጤት መስራት እንደሚገባ በመግለጽ ለኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ ስኬታማነት የሁሉም ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ የማኔጅመነት አባላቱ ለሌላው ሰራተኛ አርአያ በመሆን ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡