የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር አመራርና ሠራተኞች 26ኛውን የግንቦት ሃያ የድል በዓል አከበሩ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር አመራርና ሠራተኞች 26ኛውን የግንቦት ሃያ የድል በዓል “የሕዝቦችን እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት እየገነባች ያለች አገር - ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በኢስቲትዩቱ ዋና መሥሪያ ቤት በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የግንቦት ሃያ ድልን ተከትሎ በተፈጠረው የሕገ-መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትና ይህን ተከትከሎ በተፈጠሩ አገራዊ  ውጤቶች ዙሪያ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦ አጠቃላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቀጣይ ሕዝባዊ ተሳትፎ ከግብ ለማድረስ የኢኒስቲትዩቱ ሠራተኞች ቃል የገቡበት ስነስርዓት ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ ክብረ በዓሉን በከፈቱበት ወቅት ለግንቦት ሃያ ድል መነሻ የሆኑት አበይት ምክንያቶች ቀደም ሲል የነበሩት ሥርዓቶች የጭቆና አገዛዝን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው በኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ውጤት ማምጣት ሳይቻል መቆየቱንና ይህም አገሪቱ በልማት ጎዳና እንዳትገሰግስ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፣ የአገራችን ህዝቦች ያደረጉት ህዝባዊ ትግልና መስዋትነት በግንቦት ሃያ ለተጎናጸፍናቸው ድሎች መነሻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በጋራ መከባበርና እኩልነት ላይ የተመሠረተ ሕግ መንግሥት በማርቀቅና ፌዴራላዊ ሥርዓት በመገንባት የተጀመሩት የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የልማት እንቅስቃሴዎች ዛሬ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣በመሠረተ ልማት ዝርጋታና በሌሎችም ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ማስገኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይም የግብርናው ዘርፍ በተመለከተ ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት 52 ሚሊዬን ቶን የነበረውን ዓመታዊ የሰብል ምርት መጠን ወደ 271 ሚሊዬን ቶን ማድረስ መቻሉ፣ የተለያዩ ሰብሎችን የምርታማነት መጠን በተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች ማሳደግ መቻሉ፣ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሰብል ዝርያዎችን ከአመራረት ዘዴያቸው ጋር ማውጣት መቻሉ በግንቦት ሃያ ድል ለተገኙ ድሎች ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አገራዊ የምርምር ሥራዓቱን በተመለከተ ቀደመ ሲል አገሪቱ ትከተል የነበረው አኃዳዊ የምርምር ሥርዓት በፌዴራላዊ ሥርዓት መተካቱ፣ ከዙህ ጋር በተያያዘም የምርምር ማዕከላት በብዛትም ሆነ ባላቸው የተማረ የሰው ኃይል መጠን እያደጉ መምጣታቸውን ለአሠራርና ለተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ተያያዥ ውጤቶች መገኘት የማይተካ ሚና እንደነበረው ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡

ከቴክኖሎጂ አቅርቦት ባሻገር በቴክኖሎጂ ሠርቶ ማሳያና ማስተዋወቅ ሥራዎች ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸው በአርሶና አርብቶ አደሩ ኑሮ ላይ ለውጥ በማምጣትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ዓይነተኛ ሚና የነበራቸው መሆኑንና ኢ/ግ/ም/ኢ በተደጋጋሚ የተለያዩ ሽልማቶችና ዕውቅናዎችን ማግኘት መቻሉ የዚህ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በምርምር ተቋማት ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉ ተመራማሪዎችም በያሉበት ሆነው መልካም የሥራና የልማት ዕድሎችን በመጠቀም ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት መጠነ ሰፊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ወደፊትም የመተካካት መርሆችን በመከተልና ባህሉንም በማዳበር የምርመሩን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህም የለውጥ ሥራን በትክክለኛ አቅጣጫ በመምራት ዘርፉ ለአገር ጠቃሚ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡

ቀጣዩ ትውልድም በግንቦት ሃያ ማግሥት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል በየዘርፉ የተጀመሩትን መልካም የልማት ግስጋሴዎች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነትና የሥራ ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

በበዓሉ ላይ የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን ለድሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ ሕዝቦች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡ በቀረበው ጽሑፍ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰብን አስመልክቶ አጭር ሪፓርት በአቶ ፍስሐ ዘገየ፣ የሕዝብ ግንኙነትና አእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ዳይሬክተር ቀርቦ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት አማካይነት የተዘጋጀውን የቶንቦላ ትኬት ሠራተኞች እንዲገዙ በማድረግ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡