As a national research institute, EIAR aspires to see improved livelihood of all Ethiopians engaged in agriculture, agro-pastoralism, and pastoralism through market-competitive agricultural technologies.

Latest News

EIAR IN THE MEDIA

  

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለስምንት ተመራማሪዎች የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጠ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተለያዩ ችግር ፈች የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀትን በማመንጨትና በማቅረብ ለአገራዊ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማደግ፣ ለአርሶና አርብቶ አደሩ የገቢ ምንጭ መበራከት፣ ለምግብና ሥነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ በአጠቃላይም ለአገራዊ የግብርና ዘርፍ ዕድገት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተና እየተጫወተ የሚገኝ አገራዊ ተቋም ነው፡፡ በአገር ደረጃ ለተቀመጡ የግብርናው ዘርፍ ግቦች መሣካት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ምንጨታና አቅርቦት ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ምርምሩን ውጤታማ ለማድረግ በምርምር ቁሳቁስ፣ በምርምር ሰው ኃይል፣ በምርምር መሠረተ ልማት የምርምር አቅም ግንባታ ማድረግ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍና እንደ አገር ልናሳካ ከምንገፈልጋቸው ግቦች እውን መሆን መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ረገድ በምርምር ሰው ኃይል በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸውንና አገራችን ዛሬ ለደረሰችበት የግብርና ዕድገት ውጤት ዕድሜያቸውን ሰውተው ያለተቆጠበ አስተዋጽዖ ሲያደርጉ የቆዩና እያደረጉ የሚገኙ አንጋፋ ተመራማሪዎች ለእነዚህ ግቦች መሳካት የማይተካ ሚና ያላቸው መሆኑ እሙን ነው፡፡ 

ይህን መሠረታዊ ጉዳይ ከግምት በማስገባትም የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተቋሙን ለረጅም ዓመታት በሙያቸው ሲያገለግሉ ለቆዩና በማገልገል ላይ ለሚገኙ ሰምንት አንጋፋ ተመራማሪዎች በአገራችን የምርምር ሥርዓት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡ ዕወቅናው በተቋም ደረጃም ሆነ በአገራዊ ምርምር ሥርዓቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በማገልገል በአገር ደረጃ ጥቅም ላይ ለዋሉ የግብርና ቴክሎጂ ትሩፋቶች መገኘት ጉልህ አስተዋጽዖ ላደረጉትና ሰፊ ተሞክሮና ክህሎት ላላቸው ለእነዚህ ተመራማሪዎች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖና ላሳዩት ግንባር ቀደም የመሪነት ሚና ዕውቅና በመስጠት በምርምር ሥርዓቱ ጠብቆ ማቆየትንና ክህሎታቸውንና ልምዳቸውን በተገቢው ደረጃ ለተተኪ ተመራማሪዎች ለማስተላለፍ የሚችሉበትን ሥርዓት መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ 

“በግብርና ምርምር ለግብርና ልማት ላበረከቱት የላቀ አስተዋፆና የተዋጣለት አገልግሎት” በሚል ርዕሰ-ዕውቅና ሚያዚያ 18 ቀን 2009 ዓ/ም በተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ ዕውቅና የመስጠት ሥነ ሥርዓት ላይ ኢንስቲትዩቱን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉና ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለምርምሩ ዘርፍ መጎልበት ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የተነገረላቸው ዶ/ር ክበበው አሰፋ፣ ዶ/ር ችሎት ይርጋ፣ ዶ/ር ገመቹ ቀነኒ፣ ዶ/ር ጌትነት አሰፋ፣ ዶ/ር ታዮ ቁፋ፣ ዶ/ር ጌትነት አለማው፣ ዶ/ር ከማል ዓሊ እና ዶ/ር ጋሻዉበዜ አያሌው በአገሪቱ የግብርና ምርምር ሥርዓት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ በይፋ አግኝተዋል፡፡ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማቶቻቸውንም ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ካሱ ኢላላ እጅ ተቀብለዋል፡፡ 

የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ በተመራማሪዎች የዕድገት መሠላል ከከፍተኛ ተመራማሪ ቀጥሎ የሚሰጥ የመጨረሻው ትልቅ ደረጃ ሲሆን፤ ተመራማሪዎች በምርምር ሥርዓቱ ያበረከቷቸው ውጤቶች፣ ለህትመት ያበቋቸው ጽሑፎች፣ ማህበረሰቦችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግና በማህበረሰብ አቅም ግንባታ ረገድ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች እንዲሁም በምርምር ሥርዓቱ ውስጥ በምርምር ሥራ አመራር የነበራቸው ድርሻ ተገምግሞ የሚሰጥ ነው፡፡ 

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና በጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ ለተመራማሪዎቹ የተሰጠው ዕውቅና ተመራማሪዎቹ ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት ለተተኪዎችቻው ማስተላለፍ የሚችሉበትን አበረታች ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዕውቀትና ልምድ ሽግግሮች የግብርናውን ዘርፍ የማዘመንና የአገሪቱን ከድህነት ተላቆ ወደ ብልጽግና የመሸጋገር ራዕይ ካማሳካት አኳያ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንና በዚህም ረገድ ከመሪ ተመራማሪዎችና ከአዳዲስ ተተኪዎቻቸው የሚጠበቀው ውጤት ከፍተኛ መሆኑ ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡ 

የዕውቅና ሥነ ሥርዓቱን የከፈቱት የኢ/ግ/ም/ኢ ዋና ዳሬይክተር ዶ/ር ፈንታሁን መንግሥቱ በበኩላቸው ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ቁልፍ ችግሮች በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በመፍታት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ የማሻገር አገራዊ ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን በማስታወስ የምርምር ሰው ኃይል ግንባታ በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደበረው አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ የደረጃ ዕድገት የተሰጣቸው ተመራማሪዎችም ሥራቸውን ዓለም የዕድሜ ልክ ሙያ አድርገው በመውሰድ ጊዜና ሰዓት ሳይገድባቸው ከራሳቸው ይልቅ ህብረተሰብን በማስቀደም የተለያዩ ረጅም ውጣ ውረዶችን በማለፍ የገጠሩን ብሎም አጠቃላይ የአገሪቱን ማኅበረሰብ ህይወት ለመቀየር ብርቱ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የምርምር ውጤቶች በግብርናና በግብርና ኢንደስትሪ ልማት ዕድገት ደምቆ የሚታይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ የመጡ ከመሆናቸው አኳያም ለዚህ ስኬት በግንባር ቀደምትነት አስተዋጽዖ ላደረጉ ተመራማሪዎች ተገቢውን ደረጃ፣ ክብርና ማበረታቻ መስጠት ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የተሰጠው ዕውቅና በቀጣይ ዓመታት ምርምሩ በምርምር አሠራር፣ በምርምር ትኩረትና ተደራሽነት ለየት ባለና በላቀ አቅጣጫ እንዲጓዝ በታለመው መሠረት ወጣት ተመራማሪዎች ተቋሙ በቀጣይ ከምርምር ወደ ፈጣን የኢኖቬሽን ምዕራፍ እንዲሸጋገር፤ የግብርናና የግብርና ኢንዱስትሪ ልማት ችግሮችን በብቃት በመፍታት ዘርፉን ለማዘመን እንዲያግዝ በተነሳሽነት እንዲሰሩና በተጓዳኝ አቅማቸውን በማሳደግ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት የሚችሉበትን ዕድል እንዲፈጥሩ የማናሳሳት ሚና አንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ 

አገሪቱ ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት ተላቃ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን እንድታረጋግጥ፤ ከዚህም ባለፈም ቴክኖሎጂን ኤክስፖርት በማድረግ ምርምሩ ገቢ አመንጪ ጭምር እንዲሆን የሚያደርጉ ብቁና ተወዳዳሪ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች የሚፈጠሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ካሱ ኢላላ በበኩላቸው ተመራማሪዎች የጀመሯቸውን ለውጦች በላቀ ውጤት የማስቀጠል ኃላፊነት ያለባው መሆኑን በማስታወስ ተተኪ ተመራማሪዎችም የተሻለ በመሥራት የአገራቸውንና የህዝባቸውን የልማት ጥሪ የመመለስ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡  የምርምር ሥርዓቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት ደረጃ ላይ በማድረስ ረገድም የሚኖራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን በመገነዘብም ለዘርፉ ውጤታማነት ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢንስቲትዩቱና የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የፌዴራልና የክልል የምርምር ተቋማትና ማዕከላት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎችና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

 

 

 

 

 

Upcoming Events

 • AGPll Project Activities Planning

  Organizer: AGP ll Project

  Venue: EIAR HQ, Training Hall

  From:  June 4-7, 2018

 • TAAT Wheat Project Launching Workshop and Seed Training

  Organizer: SARD SC Project

  Venue: EIAR HQ, Hiruy Hall

  From:  June12-15, 2018

 • Agricultural Knowledge Learning Documentation and Policy Annual Mechanization Forum

  Organizer: Agricultural Mechanization Research Directorate 

  Venue: EIAR HQ, training Hall

  From:  June18, 2018

Research Areas

Research Centers