የግብርና ዕድገት ፕሮግራም የእርሻ ትራክተሮችና ተሽከርካሪዎች አከፋፈለ

የግብርና  ዕድገት ፕሮግራም በዓለም ባንክና በሌሎች ተቋማት የሚደገፍ ፕሮግራም ነው፡፡ ይኸው ፕሮግራም ብዙ ዘርፎችን ይዞ በኢትዮጵያ  የሚንቀሳቀስ ሲሆን አንደኛውና ዋነኛው የግብርና ዕድገት ፕሮግራም የምርምር ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ቴክኖሎጂ የማመንጨት፣የዘር ብዜት እና የአቅም ግንባታ ድጋፎች እያደረገ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከክልል የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ ዘርፍ ነው፡፡  

የፕሮግራሙ የምርምር ዘርፍ በቅርቡ በ2,549, 462.39 የአሜሪካን ዶላር የተገዙ 30 ትራክተሮችና 40 የመስክ ተሽከርካሪዎች ለኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ለአምስት(ለኦሮሚያ፣ ለአማራ፣ለደቡብ፣ ለትግራይ እና ለጋምቤላ) ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች አሠራጭቷል፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአገሪቷ የሚገኙ የግብርና ምርምር ሥራዎች ላይ የሚታየውን የእርሻ መሣሪያዎች እና የመስክ ተሽከርካሪዎች እጥረት በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፍ ይታመናል ተብሏል፡፡

በዚሁ መሠረት በቀጣይም በዚሁ ፕሮግራም በቅርቡ የሚገቡ ቁጥራቸው 40 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች እንዳሉም በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዲሪባ ገለቲ ገልፀዋል፡፡