በጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የሰሊጥ ዝርያዎች ማስተዋወቂያ የመስክ ቀን ተካሄደ

 

 

የአማራ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከክልሉ የተገኙ የተሻሻሉ የሰሊጥ ቴክኖሎጂዎች ማስፋፊያ የመስክ ቀን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆና በጠገዴ ወረዳ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

 

የጎንደር የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ፀዳሉ ጀምበሩ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ማዕከሉ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከክልሉ የተገኙ ምርጥ ዝርያዎችን መሠረት በማድረግ የአካባቢውን የሰሊጥ ምርታማነት ቀደም ሲል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሣይጠቀሙ በባህላዊ አስተራረስ ብቻ በሄክታር ይገኝ ከነበረው ከ2 እስከ 4 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ማሣደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለአካባቢው ምርታማ የሆነውና በብዛት የሚጠቀሙት ዝርያ 1ኛ ሁመራ-1፣ 2ኛ ጎንደር-1፣ 3ኛ ሂርሂር ዝርያን ሲሆን የዘር መጠን በሄክታር 2 ኪ/ግ እንዲሁም የማዳበሪያ መጠን 65 ኪ/ግ ዩሪያ ለየዝርያው እንደተጠቀሙ ገልፀዋል፡፡ አቶ ፀዳሉ እንደገለፁት ሥራው በዋናነት በአነስተኛ እርሻዎች ላይ የየተከናወነ ሲሂን ለተሠሩት ሥራዎች የተቀናጀ ጥረት ያደረጉ አጋሮችን ማለትም የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን፣ የሰሊጥ ምርትና ግብይት መረብን (SBN)፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን (ATA) እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡

 

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው በግንባታ ላይ የሚገኙ የግብርና ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት ሀገሪቱ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት እንደሚያስፈልጋት ጠቅሰው መንግስት አርሶ አደሮችን በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ በመስኖ ታግዘው እንዲያመርቱ ለመርዳት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም አርሶ አደሮች ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ምርቶችን ከማምረት፣ እንደ ማሾ ያሉ አዳዲስ ሰብሎችን ከማስተዋወቅ እንዲሁም ከቅባት እህሎች ምርት ተገቢውን ጥቅም ከማግኘት አንፃር በባለሙያ የታገዘ አሰራር ተከትለው አመርቂ ምርት ማምረት እንዲችሉ ማድረግ እንዲሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

 

ሰሊጥን ከአኩሪ አተር እና ከማሾ ጋር በፈረቃ መዝራት ምርታማነትን እንደሚጨምር ዶ/ር ተሾመ ዋሌ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተር በሣንጃ ወረዳ የአኩሪ አተር የእርሻ ማሣ በተጎበኝበት ወቅት ገልፀዋል፡፡ አኩሪ አተር እና ማሾ በቀጣይ በክልሉ እንዲሁም በሃገሪቱ ገበያ ተኮር  ምርቶች እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡ አክለውም አኩሪ አተር ብዙ ጥቅሞች ያሉት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተመቸ እና የአፈር ለምነትን በማሻሻል ጠቃሚ ሚና መጫወት የሚችል ሰብል ሲሆን በተጨማሪም ዘይትን ለማምረት ግብዓት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ የአኩሪ አተር ምርትን ለመጨመር ሙሉ ቴክኖሎጂን እንዲሁም በምርምር የተረጋገጠ ዘርን በመጠቀም በአንድ ሄክታር እስከ 30 ኩንታል ድረስ ማምረት እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የተሻሻሉ ዘሮችን መጠቀም እንዲሁም የተሻሻሉ የአኩሪ አተር ቴክኖሎጂዎችን ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በምርምር የወጡ ዝርያዎችንና በቴክኖሎጂ የታገዙ የሰሊጥና የአኩሪ አተር አመራረት ቴክኖሎጂን የተከተሉ አርሶ አደሮች ማሣ ተለምዷዊ አሠራርንና ዝርያን በመጠቀም አርሶ አደሮች በሰሊጥ ከሸፈኗቸው ማሣዎች ጋር በንፅፀር እንዲጎበኙ በማድረግ በመቀንጨር የታየውን ልዩነቱን ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን በቀጣይ እነዚህ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርን በመምረጥ ቴክኖሎጂን እየተከተሉ ማምረት እንዲችሉ ምክረሃሳብና ገለፃዎች ተሰጥተዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአስተዳደርና አቅም ግንባታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ችሎት ይርጋ ተቋሙ ማንኛውንም ዓይነት ተገቢ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸው በምርምር የወጡ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን የክልሉ አርሶ አደሮች መጠቀም እንዳለባቸው አበክረው አስረድተዋል፡፡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ምርጥ የምርምር ዝርያዎችን አለመጠቀም በምርት ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖም ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ክልሎች በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የምርምር ሙከራ ተደርጎላቸው የሚወጡትን ዝርያዎችና የአመራረት ቴክኖሎጂዎች ተጠቅመው የተሻለ ውጤት ማግኘት  እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

 

ከአካባቢው ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮች፣ ተሳታፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ ተመራማሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ይገኙበታል፡፡

 

·   በግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት ውስጥ ስላለው ችግር ማለትም እስካሁን ብዙ ቢከናወንም የተጠበቀውን ያህል ለውጥ አለመምጣቱ፤  የሃገርና የክልል መንግሥታት ለግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው፤

·  የኤክስቴንሽን ሠራተኞች በየጊዜው ከሥራ መልቀቅ እና ሥራ መቀየር ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑ፤

·   አንዳንድ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም አሁን ያለው ቴክኖሎጂ የበለጠ እንዲያመርቱ አለመፍቀዱ፤ ይሄውም ለአነስተኛ አርሶ አደሮች መፍትሔ ሊኖረው እንደሚገባ፤

·  የአርሶ አደሮች የስራ ባህል መቀየር እንደሚያስፈልጋቸው፤ የአርሶ አደሮች የአመለካከት ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት፤ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን እንደ ትርፍ ነገር ሣይሆን እንደ ዋና ሥራ ማየት እንዳለባቸው፤

·  የግብርና ምርምር ማዕከላት ችግርን መቋቋም ማለትም የዝናብ መብዛትን እንዲሁም ድርቅ መቋቋምን የሚችሉ ዝርያዎችን ማፍለቅ እንደሚገባቸው፤ በተጨማሪም በዘር ወቅጥ የሰሊጥ ዝርያዎች እንዳይበተኑ የሚረዱ ዝርያዎችን ማውጣት ቢችሉ፤

·         የተባይ መከላከያ ኬሚካሎችን አርሶ አደሮች በቅርብ ማግኘት እንደሚገባቸው፤

·  አርሶ አደሮች መሬት ቢኖራቸውም በአግባቡ አለመጠቀማቸው እና ጦም ማሣደራቸው፤

· በመሬታቸው ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው አጥጋቢ ምርት አለማግኘታቸው፤

·         የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በአርሶ አደሮች እጅ በአግባቡ አለመድረሣቸው፤

·         በአሁኑ ጊዜ የሰሊጥ ምርታማነት በጣም ውስን መሆኑ፤

·      ባለድርሻዎች እና አጋሮቻቸው አርሶ አደሮችን ለመለወጥ የሚያደርጉትን ትብብር እና ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው፤

·         የድጋፍ ትኩረት የሚሰጠው ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ብቻ መሆኑ፤

·  ለትላልቅ አርሶ አደሮች ትኩረት ይሰጥ፤ መንግስት የግብርና ግብዓቶችን፣ ፋይናንስ፣ ግብይትን፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን እና የደህንነት ጉዳዮች ችግሮች ላይ ትኩረት ይስጥ በሚሉት ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የመስክ ቀን ጉብኝቱ ተጠናቋል፡፡