ኢንስቲትዩቱ ከኦሮሚያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጋር የተቀናጀ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ማስፋት ሥራ እያከናወነ ነው

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ከተልዕኮው በመነሳት ለአገሪቷ የግብርና ዕድገት ለሚያበረክተው ጉልህ አስተዋፅኦ በስሩ በሚገኙ የምርምር ማዕከላት አማካይነት ከሚያደርጋቸው የምርምር ስራዎች በተጨማሪ የክልል የግብርና ምርምር ተቋማትን በማስተባበር በተመረጡ አካባቢዎች ላይ በጋራ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ማስፋት ስራዎች ያከናውናል፡፡

በዚሁ መሠረት ከኦሮሚያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት (IQQO) በመተባበር በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ 81 ሄክታር መሬት ላይ እያከናወነ ያለውን የተቀናጀ የብቅል ገብስ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መስከረም 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የአርሶ አደር የመስክ ቀን አካሂዷል፡፡

ይሄው የብቅል ገብስ ቴክኖሎጂ (ዝርያ) “ኢቦን” የተሰኘ ሲሆን መገኛው በኢንስቲትዩቱ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ሲሆን በዋናነት በቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የማባዛት ሥራው እየተሰራ ይገኛል፡፡ የመስክ ጉብኝት የተካሄደበት የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚገኘው የብቅል ገብስ ቴክኖሎጂ የማስፋት ሥራ ከተመረተ በኋላ ለዘር ብዜት እንደሚውል የማስፋፋት ስራውን በክላስተር ተደራጅተው እያከናወኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ የሚከናወኑ የምርምርና የቴክኖሎጂ ማስፋት ሥራዎች አርሶ አደሩን በስፋት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር በአገሪቱ የሚገኙ የቢራ ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሪ የሚያስገቡትን የብቅል ገብስ በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ 

የብቅል ገብሱን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት የሚሰጠውና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አንዱና ዋነኛው ተግባር ሲሆን የግብርና ቴክኖሎጂ በአንድ ተቋም ወይም በጥቂት ተቋማት ተሳትፎ ብቻ የሚተገበር ስራ ባለመሆኑ ያለውን ኃብት በተደራጀ ሁኔታ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና ትስስር መፍጠር እንሚገባ ተገልጿል፡፡ የሁለቱ ተቋማት በቅንጅት ቴክኖሎጂን  የማስፋት ጅምር ሥራዎች ለዚሁ ማሳያ መሆናቸውና ለዚህም ተጨማሪ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡ 

በመስክ ቀን ጉብኝቱ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሣትፈዋል፡፡