የአገራችን ግብርና ከእኛ እስከ ነጩ የግብርና አብዮት

 ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ ይባላሉ፡፡ በምዕራብ አርሲ ሽርካ ወረዳ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የተገኙት፡፡ ተወልደው ያደጉበት የገጠር ማህበረሰብ እንደ አብዛኛው የአገሪቱ ነዋሪ በግብርና ስርዓት ውስጥ የሚተዳደር መሆኑ ለአሁን ማንነታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ይናገራሉ፡፡ በትውልድ ቀይአቸው በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአንጋፋው ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000ዓ.ም ከቤልጂየም ጌንት ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡ 

ዶ/ር አስናቀ በተሰማሩበት የግብርና መስክ ለረጅም አመታት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ የቆዩ ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተመራማሪነትና በሃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከልንም በዳይሬክተርነት ሲመሩ ቆይተዋል፡: በተጨማሪም የብሄራዊ የቴክኖሎጂ ስኬሊንግ አፕ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በአሁን ወቅትም በዓለም አቀፍ የከፊል ደረቃማ አካባቢዎች የሰብል ምርምር ኢንስቲትዩት (ICRISAT) በተመራማሪነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ80 በላይ የሣይንስ ፅሁፎችንና የግብርና ምርምር መረጃዎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ የምርምር አካላት ጋር በመሆን በመፅሄት፣ መፅሃፍት እና ፕሮሲዲንጎች መልክ ማሳተም ችለዋል፡፡ 

የሳይንስ ተመራማሪዎች እውቀትና ልምድ በየዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚችል መሆን ይኖርበታል የሚሉት ተመራማሪው በተለያዩ የሞያ መስኮች በመሰማራት እውቀትና ልምድን ያዳበሩ ባለሞያዎች ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ችግር ፈቺና መፍትሄ አመላካች የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ያምናሉ፡፡ ይህም  አገሪቱን ወደኋላ በመጎተት ለዘመናት ሲፈታተን የቆየውን የድህነትና ኋላ ቀርነት ገመድ ቀስ በቀስ ገዝግዞ ለመጣል አይነተኛ መፍትሄ ነው ይላሉ፡፡

በዚህ መነሻነትም ነው ተመራማሪው “የአገራችን ግብርና ከእኛ እስከ ነጩ የግብርና አብዮት“በሚል ርዕስ ሳይንሳዊና ስነፅሁፋዊ ለዛ ያለው የግብርና መፅሀፍ በመፃፍ ለህትመት ያበቁት፡፡ ሳይንሳዊ መፅሃፉ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም ለምርቃት የበቃ ሲሆን በምርቃት ስነስርዓቱ ላይም በርካታ ነባርና አዳዲስ የግብርና ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

የመፅሃፉ ይዘት የግብርናን ሳይንስ ከአገሪቱ ተጨባጭ የግብርና ስርዓት ጋር በማዛመድ የሃሳብ ውይይት (dialogue)የሚያነሳ ሲሆን ፀሃፊው የአገሪቱን የግብርና ስርዓት፣ አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሞያውና ሌሎችንም በግብርናው ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንደ መነሻ በማድረግ ከግብርና ሳይንስ የወሰዷቸውን እውቀቶችና ልምዶች እንዲሁም ከልጅነት ጀምሮ የተመለከቷቸውንና ያለፉባቸውን የአገሪቱ የግብርና ስርዓት እውነተኛ ገፅታ ምን እንደሚመስል በትረካና አሳታፊ በሆነ አቀራረብ ግልፅ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን  በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮችም ላይ የግብርናውን ሳይንስና ገሀዱን አለም ያጣመረ ሰፋ ያለ ትንታኔ ይሰጣል፤ አንባቢያን  የራሳቸውን መደምደሚያ ሃሳብ እንዲያቀርቡም ለውሳኔ ክፍት በማድረግ ወደ ሌላ ርዕሰ ሃሳብ ይሻገራል፡፡

በሰብል በእንሰሳት በደንና ተፈጥሮ ሃብቶች ዙሪያ ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትና ልንጠቀምባቸው የሚገቡ የወደፊት እድሎችን የሚጠቁመውን ይህን መፅሃፍ በመፃፍ ሂደት ውስጥ የግብርና ሳይንስን ከስነ-ፅሁፍ ጋር ለማስማማት እንዲሁም በአገራችን የቋንቋ ፍቺ ውስጥ ቀጥተኛ ወይም ተኪ ቃል የሌላቸውን ሳይንሳዊ ቃላትን ለሁሉም ማህበረሰብ ክፍል በሚገባ መልኩ ተርጉሞ ወይም በተቀራራቢ ቃላት ተክቶ ማቅረቡ አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም መፅሃፉ አንባቢያን ጋር ደርሶ ሊያመጣ የሚችለውን አዎንታዊ ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ ጥረትና ጥንቃቄ የቃላት መረጣ፣ ስብጥርና ውህደት በማካሄድ ለዛ ያለውና ማራኪ የአፃፃፍ ሂደትን የተከተለ የስነ-ፅሁፍ ውጤትን ማቅረብ ችለዋል፡፡

ፀሃፊው የአገሪቱን ግብርና ዘርፍ ለዘመናት ስልጣኔ ሳያሳይ እድገትን ያስመዘገበ ዘርፍ በማለት ይገልፁታል፡፡ ለዚህም በርካታ ማሳያዎችን በመፅሃፉ ውስጥ ያሰፈሩ ሲሆን በማደግ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ እንዴት ማዘመን ይቻላል የሚል ጥያቄን በአንባቢው አእምሮ ውስጥ ይፈጥራል፤ ችግሮችን ነቅሶ ያወጣል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ያመላከታል፤ ለዘርፉ መዘመን የሚሰሩ ባለሞዎችም መፅሃፉ ጠቋሚ ሃሳቦችንና መረጃዎችን አዝሏል፡፡

ሳይንሳዊ ጽሁፎችን በመፅሃፍ መልክ አቅርቦ ለንባብ ማብቃት እምብዛም የተለመደ ነገር ካለመሆኑ በተጨማሪ አንድን ሳይንሳዊ መፅሃፍ ለንባብ ለማብቃት የሚወስደው ጊዜ ከሌሎች ዘርፎች አንፃር ሲታይ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማውጣት የሚወስደው ጊዜ ረጅም መሆኑና እነዚህን መረጃዎች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት በመጠየቁ እንደሆነ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ሳይንስ አሻሚ ያልሆነ፣ የማያመታታ፣ ከድግግሞሽ የፀዳ፣ ግልፅና አጭር መረጃን ሲያቀርብ በሌላ በኩል  ሳይንሳዊ መረጃዎችን ሁሉም ህብረተሰብ በሚረዳው መልኩ ለማስቀመጥ የስነ-ፅሁፍ ጥበብን በመጠቀም በተብራራ ሁኔታ ማስፈርን ይጠይቃል፡፡

ሆኖም “በግብርና ሳይንስ ዙሪያ በርካታ መረጃዎችንና እውቀቶችን ለማህበረሰቡ ማድረስ ከባድ አይሆንም” የሚሉት ተመራማሪው በሃገራችን በአብዛኛው የግብርና ትምህርቶች የሚሰጡት በውጪ አገራት ማስተማሪያ መፅሃፍት ቢሆንም በሁሉም ደረጃ  ግብርናን ለሚያጠኑ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች የግብርና ማስተማሪያ መፅሀፍት በአገር በቀል የግብርና ተቋማት ውስጥ ቢዘጋጁ የበለጠ ተመራጭ ይሆናሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ የአገራችን የምርምር ፅሁፎች ከ70-90 በመቶ የሚሆኑትን ማጣቀሻ መፅሃፍት የሚጠቀሙት ከአገር ውጭ ባሉ ፀሃፍት የተፃፉትን መሆኑ የራሳችንን በማየት ላይ ትኩረት ያለመስጠታችንን አመላካች ነው ሲሉ በተጨማሪም በዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ያልተሰራበት በመሆኑ የመረጃ እጥረት ስለሚያጋጥምም ነው ይላሉ ተመራማሪው፡፡ ከትምህርት ስርዓቱ ጋርም በተያያዘ የአገራችን የግብርና ማስተማሪያ ተቋማት ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት በማንሳትም መፅሃፉ ያወያያል፡፡

“የአገራችን ግብርና ከእኛ እስከ ነጩ የግብርና አብዮት“በሚለው ርዕስ ስር “እኛ” የሚለው ስያሜ አገሪቱ አሁን ያለችበትን የግብርና ሁኔታ ሲወክል “ነጩ የግብርና አብዮት” የሚለው ደግሞ በተለይም ምዕራቡ አለም በግብርናው ዘርፍ የደረሰበትን የስልጣኔ ደረጃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማመላከት ታስቦ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ፡፡

ተመራማሪው ለፅሁፉ እንደማጣቀሻ (reference) ከተጠቀሙባቸው መካከል አንዱ የ83 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑትና ለ70 ዓመታት በግብርና ሙያ ሲተዳደሩ የቆዩት ወላጅ አባታቸው አቶ ፍቅሬን እንደሆነ በመግለፅ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ ግብርናን በቅርበት እንዲያዩትና እንዲረዱት በማስቻል ሂደት ውስጥ የወላጅ አባታቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

የግብርና  የፍላጎት ጥያቄ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ በሁሉም የኑሮና የማንነት ደረጃ የሚገኝ የአገሪቱ የህብረተሰብ ክፍል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው የሚሉት ተመራማሪው፤ በአገሪቱ ውስጥ ከ17 ሚሊየን ባልበለጡ አርሶ አደሮች ይዞታ ስር ያሉ በአማካኝ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ማሳዎች አሉ ሲሉ በመፅሃፋቸው ውስጥ ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ማሳዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ምርታማ ናቸው ወይ የሚለው የዘመናት ጥያቄ ሆኖ እንደቆየም አብረው ያነሳሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ግብርናውን ያዘምናሉ ተብለው የመጡ በርካታ አሰራሮች ቢኖሩም የታሰበውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸውን በማተት ግብርና ሰፊ፣ ጥልቅና የማያልቅ እውቀት ሊሸመትበት የሚችል ዘርፍ በመሆኑ ባለሞያዎች ጊዜ ሰጥተው ቢሰሩበት ለአገሪቱ ግብርና እድገት የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚያስችል እድል እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡

የግብርናው ዘርፍ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የትኛውም ያደጉ አገራት ኢንዱስትሪ በግብርና መመራቱ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ለሌሎች ዘርፎችም ሆነ ለግብርናው እድገት ወሳኝ የሚሆነው እርስ በርሳቸው ተያይዘው እየተመጋገቡ ሲዘምኑ እንጂ በተናጠል የሚያዋጣ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ በግብርና ውስጥ ያሉት ሶስቱ አካላት ማለትም፣ የመንግስት የግልና የምርምር ተቋማት እርስ በርሳቸው የሚኖራቸው ተመጋጋቢነት ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም መንግስት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ለግብርናው እድገት አጋዥ የሆኑ አካላት ጋር በጥምረት መስራቱ ጠቃሚ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ በሌላ በኩልም በአገሪቱ ያሉ የመንግስት ግብርና ተቋማት አሰራር ለዘርፉ አመቺ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህንንም ተመራማሪው በመፅሃፉ ውስጥ ለውይይት እነንዲቀርብ አድርገዋል፡፡

ፀሃፊው ካነሷቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ የግብርናው ደህንነትና ጥበቃ ጉዳይ ሲሆን ግብርናውን ፈተና ውስጥ ሊጥሉ ከሚችሉ የውስጥና የውጭ እንዲሁም ህያውና ኢህይወታዊ ደንቢዎች (biotic and abiotic factors) መጠበቅ እንዳለበት ይጠቁሙበታል፡፡ አሁን ያለው የግብርና አሰራር ለተተኪው ትውልድ ወይንም ወጣቱ ሳቢ ያለመሆኑን በመጥቀስ ለነገው የግብርና ማህበረሰብ ግንባታ አሰራሮችን አመቺ በማድረግ በግብርና ዘርፍ የወጣቱን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻልና በሌላ ጎኑ ወደ ከተማ የሚኖርን ፍልሰት ለመቆጣጠር እንደሚረዳም ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም አዲሱ የግብርና ትውልድ በማለት ፀሃፊው ለሚገልፁት የዘመኑ ግብርና ሁኔታ አመቺ የሆኑ አሰራሮች ሊፈጠሩ ይገባል ይላሉ፡፡

በመፅሃፍ ምረቃው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ ከአርቲክሎች ባሻገር መፅሃፍ የሚያሳትም የግብርና ተመራማሪ ማፍራት ዋነኛ የምርምር ስርዓቱ ፍላጎትና ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በመግለፅ የምርምር ውጤቶችን በመፅሃፍ ደረጃ አሳትሞ ለግብርናው ማህበረሰብ ማቅረብ በቂ እውቀትና ልምድ የሚጠይቅ በመሆኑ በምርምር ሂደቱ በርካታ አመታትን ያሳለፉና በቂ እውቀትና ልምድ ያካበቱ ተመራማሪዎችን አይን በመክፈት ከምርምሩ ባሻገር እምቅ የሆነ እውቀታቸውን ለማህበረሰቡ የሚያጋሩበትን መንገድ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

በምርምር ስርዓቱ ውስጥ ለረጅም አመታት ያሳለፉ ተመራማሪዎች በርካታ የምርምር መረጃዎችን በፅሁፍ መልክ እንደሚያስተላልፉ ቢታወቅም በተደራጀና ሙሉ መረጃ በሚሰጥ መልከ ማቅረብን ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ያነሳሉ፡፡ ይህንንም ልምድ ለማዳበር የምርምር ሳይንስን በስነፅሁፍ ቃና በማዋዛት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊገነዘበው በሚችል ቋንቋና ይዘት ለማቅረብ የሚረዱ የተለያዩ ስልጠናዎች ለሳይንሱ ማህበረሰብ መቅረብ እንደሚኖርባቸው አስምረዋል፡፡ በዚህም ኢንስቲትዩቱ ሳይንስን በስነ ፅሁፍ ዘዬ አዋዶ እንዴት ለአንባቢያን ማቅረብ አንደሚቻል የሚያስረዳ የስልጠና መርሃ-ግብር ለነባርና አዲስ ተመራማሪዎች ለማዘጋጀት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡