የግብርና ተቋማት ጥምረት ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት

 

በአገር አቀፍ ደረጃ በምርምር የሚወጡ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ስርጭት ሂደት ፈጣንና ወቅቱን የጠበቀ ሲሆን የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገው መልኩ እንዲዘምን ምክንያት ከመሆኑም በተጨማሪ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለግብርና ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት እንዲሁም ለወጪ ንግድ አቅርቦት የሚውል የግብርና ምርት ማምረት ያስችላል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአራቱ የክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች ማለትም የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የትግራይና ደቡብ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች ጋር በመቀናጀት አዳዲስና ውጤታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ ተጠቃሚዎች ዘንድ በተሳካ ሁኔታ እንዲደርሱ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል የጥምረት ስራ ለማከናወን የሚረዳ ፕሮጀክት በመንደፍ ወደ ተግባር መግባት የሚያስችል የጋራ የውል ስምምነት መጋቢት 3 ቀን 2010 . አካሂደዋል፡፡

ተቋማቱ ይህንን የውል ስምምነት በመፈፀም ወደ ተግባር ለመግባት ያስቻላቸው በአገሪቱ በግብርና ዙሪያ እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች፣ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን እንዲሁም የግብርና ኤክስቴንሽን ሂደቱን ለማጠናከር በተካሄደ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ መነሻነት መሆኑ ተገልፃል፡፡ በዚሁ ሰፊ የግብርና ልማት ስራ ውስጥም ከፌደራልና ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች በተጨማሪም የክልል የግብርና ቢሮዎች፣ የዞንና የወረዳ ግብርና መምሪያና ገጠር ልማት /ቤቶች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በቅንጅት ስራው አተገባበር ዙሪያም ባለድርሻ አካላቱ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም ከበጀት ጀምሮ በባለሞያ ተደጋጋሚ ድጋፍና እገዛ እንዲሁም በቴክኖሎጂ አቅርቦት ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በኩታገጠም ለተደራጁ አርሶ አደሮች የሚፈለገውን ምርት ለማምጣት የሚያስችሉ ዘዴዎችን ተጠቅመው ማምረት እንዲችሉ የሚያግዛቸውን ሞያዊ ስልጠና በመስጠት ሂደትም ተካፋይ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ካቀዳቸው የክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች መካከልም የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አንዱ ሲሆን፣ ተቋማቱ የትኩረት አቅጣጫቸው ያደረጉት በኦሮሚያ ክልል በባሌ፤ በምእራብ አርሲ፣ ሆሮጉዱሩ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እና በፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞኖች ውስጥ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ በምርምር የወጡ የተሻሻሉ የአሰራር ሂደቶችን በመከተል የሰብል ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ በማስፋፋትና ፍላጎት በመፍጠር አርሶ አደሩ ዘንድ ተደራሽ ማድረግ ላይ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም እንቅስቃሴው በተጠናከረና እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲቀጥል የሚያግዙ ሞያዊ ስልጠናዎችን ለተሳታፊ የግብርና ባለሞያዎች እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡

በሆሮጉዱሩ ወለጋ በሚገኙ ወረዳዎች የተሻሻለ የስንዴ ዝርያን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራን የተከናወነ ሲሆን በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀትና አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ የዘር ብዜት ስራ የተከናወነ ሲሆን በተመሳሳይም በምዕራብ አርሲ ዞን እንዲሁም በምስራቅ ሀረርጌና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የተሻሻለ የቢራ ገብስ፣ የስንዴና የማሽላ ቴክኖሎጂዎች በክላስተር ለተደራጁ አርሶአደሮች በማስተዋወቅ የግብርና ምርት እድገት ላይ አስተጽኦ ማድረግ መቻሉን ተመልክቷል፡፡

ጊራና-1 እና መልካም የተሰኙ በሽታንና ድርቅን በመቋቋም ምርት መስጠት የሚችሉ የማሽላ ዝርያዎችን በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቦኬ፣ ዳሮለቡ፣ ባቢሌና ፈዲስ ወረዳዎች ላይ 105.87 ሄክታር መሬት በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ስራ የተሰራ ሲሆን በተመሳሳይም ሳነቴ የተሰኘ የተሻሻለ የዳቦ ስንዴ ዝርያ በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ጂማራሬና ሆሮ ወረዳዎች 60 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር ለተደራጁ አርሶ አደሮች የማስተተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ በባሌ ዞን ውስጥ በሚገኙት አጋርፋና ጎሎልቻ ወረዳዎች 60 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር ለተደራጁ 120 አርሶ አደሮችም ኡቱባ የተሰኘ የተሻሻለ የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ ዝርያ የተዋወቀ ሲሆን በተጨማሪም በም/አርሲና ባሌ ዞኖች ውስጥ በሚገኙት ዶዶላና ዲንሾ ወረዳዎች 100 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር በተደራጁ 117 አርሶአደሮች ኢቦን 174/03 የተሰኘ የተሻሻለ የብቅል ገብስን ማምረት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተመሳሳይም ከደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ስርጸት ለማከናወን በደቡብ ክልል ቡታጅራ ከተማ ላይ በተካሄደ ውይይት ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በዚሁ መሰረትም በክልሉ በሲዳማ፣ ጋሞጎፋና ጉራጌ ዞኖች የተመረጡ ወረዳዎች ላይ የቢራ ገብስ፣ የስንዴና ጤፍ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ስራዎች እየተከናነወኑ ይገኛሉ፡፡ ለዚሁ ቅንጅታዊ ስራ የሲዳማ፣ የጋሞጎፋና የጉራጌ ዞኖች የሚገኙ አርቤጎና፣ከምባና ቸሃ ወረዳዎች የተመረጡ ሲሆን በሲዳማ ዞን አርቤጎና ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማደራጀት የተሻሻለ የቢራ ገብስ ቴክኖሎጂን ማምረት የሚያስችሏቸውን ስልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ምርት የማስገባት ስራ የተሰራ ሲሆን የአካባቢው የእርሻ መሬት አሲዳማነት ለምርታማነት እንቅፋት እንዳይሆን የኒረዳ የኖራ ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ስራም ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጉራጌ ዞን አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት የጤፍ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ማምረት እንዲችሉ እገዛ የተደረገላቸው ሲሆን በተመሳሳይም በሲዳማ ዞን በአርቤጎና ወረዳ ምንም አይነት ምርት ሳይካሄድበት የቆየ 100 ሄክታር መሬት ላይ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት ኢቦን የተሰኘ የተሻሻለ የቢራ ገብስ ዝርያን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራዎችን አከናውኗል፡፡

ከዚሁ የተቀናጀ የግብርና የቴክኖሎጂ ስርጸት ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለመሆን ከፌደራል ኢንስቲትዩቱ ጋር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ካሳዩ ተቋማት አንዱ የትግራይ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ከፌደራል ተቋሙ ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ ሊተገበሩ ስለሚችሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ማላመድና ማስፋፋት ስራዎች አተገባበር ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰፋ ያለ ውይይት በውቅሮ ከተማ አካሂዷል፡፡ በዚሁ ውይይት መነሻነትም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተካሂደው ወደ ስራ የተገባ ሲሆን በጥቂት ወራት ውስጥ በተለይም በሁመራ፣ አክሱምና አድዋ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተሻሻለ የሰሊጥና ጤፍ ቴክኖሎጂዎች የማስተዋወቅ ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማከናወን መቻሉ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለረግረጋማ አካባቢዎችና ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ መሆናቸው የተረጋገጡ ኮራና ቦሴት የተሰኙ የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን በአክሱምና አድዋ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ስራ የተከናወነ ሲሆን በአምባ አላጄ፣ ተምቤንና አላማጣ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮችም የተሻሻሉ የጤፍና የዱረም ስንዴ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና ማስፋት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

በተመሳሳይም የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በክልሉ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ስርጸት ፕሮጀክትን ለመተግበር ከኢትዮጰያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን በነዚሁ አካባቢዎች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት የአካባቢውን አርሶ አደር ህይወት ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም በተለይ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በማዕከላዊ ጎንደር በሚገኙ ወረዳዎች ያሉ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀትና ከፌደራል ተቋሙ በምርምር የተለቀቁ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች በመጠቀም ማምረት እንዲችሉ የማገዝ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የአካባቢዎቹ የእርሻ መሬቶች በከፊልና በሙሉ አሲዳማነት የሚያጠቃቸው መሆኑ በመረጋገጡ የአፈሩን አሲዳማነት ለመቀነስ የሚያስችል የኖራ አጠቃቀም መረጃን ለአርሶ አደሮች በማቅረብና በአጠቃቀሙ ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ በማስጨበጥ ውጤታማ የስንዴ ምርት ማከናወን ተችሏል፡፡ የአፈር አሲዳማነት በከፍተኛ ደረጃ ባጠቃቸው በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ የጎዛምንና ማቻክል ወረዳዎች እንዲሁም በደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኙ 191 አርሶአደሮችን 92.75 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር በማደራጀት የኖራ አጠቃቀም ምክረ-ኃሳብ ተግባራዊ ያደረገ የስንዴ ምርት በስፋት ማምረት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በማስገባት በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ የሰብል አይነቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ሰሊጥ በምርምር በመታገዝ በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚያስችል ዝርያን በማውጣት ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንዲደርስ በማድረግ የአገሪቱን የሰሊጥ ምርት ለማሻሻልና የውጭ ምንዛሬን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚህም በማዕከላዊ፣ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር በሚገኙ ሰፋፊ ማሳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ የተሻሻሉ የቢራ ገብስ ቴክኖሎጂዎችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የፌደራል ኢንስቲትዩቱ ከክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ የቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቅና ማስፋፋት እንቅስቃሴዎች ተጠናክሮ መቀጠል ለአገሪቱ የምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፍላጎት ግብዓት መሟላት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ በዚህም የተቋማቱ ቅንጅታዊ ስራ ክልሎች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሃይልና እውቀት በመጠቀም ውጤታማ የግብርና ምርት ማምረት እንዲችሉ ያገዘ ከመሆኑም በላይ የእውቀትና ልምድ ልውውጥ ሂደትን ተግባራዊ ያደረገ ሆኗል፡፡ 

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በስሩ የሚገኙ የፌደራል የምርምር ማዕከላትን በማስተባበር በሰብል፣ በእንሰሳትና በተፈጥሮ ሃብት ዋና ዋና የምርምር መስኮች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ፤ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ እንዲሁም ለወጪ ንግድ ግብዓት አቅርቦት የሚውሉ አማራጭ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማላመድ በማስተዋወቅና በማስፋፋት የግብርና ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከሌሎች የምርምርና ልማት አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአገሪቱን የግብርና እድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የበኩሉን አስተዋፅኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡