የምርምር ቴክኖሎጂ ውጤቶች ሚና በከተማ ግብርና

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርሶ አደሩን እንዲሁም አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን የአገሪቱ ማህበረሰብ ኑሮ የተሻለ ለማድረግ ብሎም የግብርናው ዘርፍ ዘላቂ እድገት እንዲያስመዘግብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። 

ኢንስቲትዮቱ የገጠሩን ማህበረሰብ ምርታማነት ከማሣደግም ባለፈ በከተማ ዙሪያ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በማስተዋወቅ አምራች እንዲሆኑ ለማስቻል እየሠራ ይገኛል ። በዚህም በምርምር የሚያወጣቸውን ከአካባቢ ስነ ምህዳር እንዲሁም አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለከተማ አርሶና አርብቶ አደሮች የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ተቋሙ ይህንን እንቅስቃሴ አጀንዳው አድርጎ መስራት የጀመረው በ2009ዓ.ም ሲሆን በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ስርፀትና ኮሜርሻላይዜሽን ምርምር ዳይሬክቶሬትም ይህንኑ ተግባር እያስተባበረ ይገኛል፡፡ 

ከከተማ ግብርና የሚገኝ ምርት የምግብ ስርዓትን በማሳደግ ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት አይነተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ማህበረሰቡ በአነስተኛ ቦታ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ የግብርና ምርቶችን በማምረት ለለት ተእለት ፍጆታው ማዋል ሲጀምር የምግብ ደህንነቱ ከመጠበቁም በተጨማሪ በምርቱ ጥራት ላይ የሚኖረው እምነት ይጨምራል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም እንደ ትራንስፖርት፣ የዘመናዊ እህል ማከማቻ ቦታ እጥረት እንዲሁም የገበያ ችግርና የመሣሠሉ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የድህረ ምርት ብክነት መንስኤዎችን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ የከተማው ማህበረሰብ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ በማድረግ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፤ በከተሞች የሚኖረው የምግብ ዋስትና ችግር ከእናቶችና ህፃናት ጤና ከፍተኛ የሆነ ትስስር ያለው በመሆኑ የስርዓተ-ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለከተማ ግብርና ልማት ስራ በሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ላይ ምርምር እንደሚሰራና ከኢንስቲትዩቱ የወጡ ከነባር የዶሮ ዝርያዎች የተሻለ የምርት ልዩነት የሚሠጡ የዶሮ ዝሪያዎች፤ ከአንድ የወት ላም በቀን ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን የወተት መጠን ማሣደግ የቻሉ የተሻሻሉ የላም ዝርያዎች ፤ እንዲሁም የተለያዩ የሠብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ቴክኖሎጂዎችም ወደ ተጠቃሚ ተሸጋግረው ማህበረሰቡ ውጤታማ ምርት ማምረት የሚያስችለውን አሰራር በመዘርጋት የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ እየሠራ ይገኛል ፡፡ በዚህም የማህበረሰቡ አካል የሆኑ በርካታ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው የስራ እድሎችን ይፈጥራል፡፡ ይህንንም እንደ መነሻ በመውሠድ ተቋሙ እነዚህን የከተማ ግብርና ስራዎች ለማስፋፋትና በምርምር ያወጣቸውን የሰብልና እንሠሣት ቴክኖሎጂዎች በስፋት ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ ከፍተኛ እንቅስቀሴዎች ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ 

ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱዩት በምርምር የሚወጡ የሰብል፣ እንስሳትና ተፈጥሮ ሀብት ቴክኖሎጂዎች በመሠረታዊነት የገጠሩን ህዝብ ያማከሉ ቢሆኑም ቴክኖሎጂዎቹ ውጤታማ በመሆን ከፍተኛ ምርት መስጠት ከሚያስችላቸው አየር ንብረትና ሌሎች ተያያዥ ግብአቶች ጋር ተቀራራቢ ስነምህዳር ባላቸው ከተማዎች እንዲሁም ከተማ ቀመስ ለሆኑ አካባቢዎች በቀላሉ እንዲላመዱ በማድረግ የሚታሠበውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ። በተለይም የተሻሻሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ቴክኖሎጂዎች፣ የእንስሳት መኖ ቴክኖሎጂዎች፣ የመዓዛማና መድሀኒት ሠብሎች፣ የዶሮ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ከተፈጥሮ ማዳበሪያና አካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ምክረ ሃሳቦችን ለከተማ ግብርናም በቀላል ወጪ እንዲሁም አነስተኛ ቦታ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን በረህ ወረዳና በዚሁ ወረዳ የተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ የሚገኘው CDCB ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የአካባበቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማስፋት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ዘር ብዜት ተግባራትን የማከናወን ሃላፊነት ወስዶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም በበርህ ወረዳ ሮጌ ቀበሌ የሚገኙ ነዋሪዎችን በክላስተር በማቀናጀት የሰንዴ ቴክኖሎጂ የዘር ብዜት ስራ ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የአርሶ አደር ማሳ ላይ የሽብምራ ቴክኖሎጂ ሰርቶ ማሳያ በማከናወን በሌሎች የአካባቢው ማህበረሰቦች እንዲጎበኝ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይም በዚሁ ወረዳ ሞጎሮ ቀበሌ የሚኖሩ የአካባቢው አርሶአደሮችን በክላስተር በማደራጀት የስንዴ ዘር ብዜት ማከናወን የቻሉ ሲሆን፣ በቀበሌው የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከል የተከናወኑ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ ሙከራዎችም ተካሂደዋል፡፡ የሰንዴና የጤፍ ሰርቶ ማሳያዎችን፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ እንዲሁም የዶሮ ምግብ ማቀነባበርያ ማዕከላትም በወረዳው በሚገኝ ለገቦሎ ቀበሌ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ 

በግብርናው ዘረፍ የሚሠሩ የተለያዩ የመንግስት ፓሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ የግብርና ተመራማሪዎች፣ የዞንና የወረዳ የግብርና ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ በከተማ ግብርና ዙሪያ የተሠሩትን ውጤታማ የሆኑ የቴክኖሎጂ ሰርቶ ማሳያና የዘር ብዜት ስራዎች በመጎብኘትና ውይይት በማድረግ ውጤታቸውን በጋራ ለመገምገምና ግብረመልስ ለማሰባሰብ እንዲሁም በኢንስቲትዩቱ፣ በወረዳውና በCDCB በቅንጅት የተሰሩትን የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ማስፋት ስራዎችን በማሳየትና ውይይት በማድረግ ቋሚ የሆነ ትስስር ለመፍጠር የሚረዳ የመስክ ቀን ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን በረህ ወረዳ ሮጌ፣ ሞጎሮና ለገቦሎ ቀበሌዎች ተካሂዷል፡፡ 

ኢንስቲትዩቱ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን የከተማ አካባቢ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ በ2010/11 መኸር ወቅት የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ ማስተዋወቅ እና አቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ እነዚህ ተግባራትም ከምርምር ማዕከል የሙከራ ጣቢያዎች ጀምሮ እስከ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ድረስ በስፋት በማሳተፍ የተከናወኑ ሲሆን አላማውም አዳዲስና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ፣ የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ስራዎችን በማካሄድንና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወንን በአገሪቱ ውጤታማ የሆነ የከተማ ግብርና ማስፋፋት ነው፡፡ ኢንስትቲዩቱ በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ልምድ በመውሰድ ለአገሪቱ ስነምህዳር ተስማሚና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉና ለከተማ ግብርና አመቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመለየት የማላመድ ስራ በመስራት ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡ ለውጤታማነቱም ተቋማዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ለተጠቃሚዎች ስልጠና በመስጠት፣ ከስልጠናም በኋላ ተገቢው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በስራ ላይ እንዲውል ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የገበያ ትስስር በመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ሆኖም የከተማ ግብርና ተግባራት ሂደት ከዚህ በተሻለ ፍጥነት ወደፊት እንዲራመድ ለማስቻል ዘርፉ በቴክኖሎጂና እውቀት ሊታገዝ የሚገባው ሲሆን ተግባራቱም በከተማ ውስጥ ባሉ አነስተኛ ቦታዎችና ተፈጥሮ ሃብት ሊተገበሩ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል ይላሉ በዘርፋ ለረጅም ጊዜያት ያገለገሉ የግብርና ባለሞያዎች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ የተጠቃሚዎችን አቅም ሊገነቡ የሚችሉ የልምድ ልውውጥና የግንዛቤ መፍጠር ስራን ማከናወን ለስራው ዘለቄታዊነት መፍትሄ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቅሳሉ፡፡  

በተለይም በዝቅተኛ የእለት ገቢ ራሣቸውን የሚያስተዳድሩ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት ቀና ድጋፍ በአነስተኛ ቦታ ማምረትና ህይወታቸውን መቀየር የሚያስችላቸውን መንገድ መፍጠር፤ የተጀመሩትንም ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።