በስንዴ ራስን የመቻል ጉዞ በፍጥነት ሩጫ ላይ

ግብርና ለአለም ኢኮኖሚ እድገት ዋነኛና ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ያለ ግብርና የሰው ልጅ ህልውና ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ በዚህም ምክንያት የአለም ሃገራት ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው የግብርናውን ሴክተር ለማዘመንና ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ከላይ እታች እያሉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ከራሳቸው ፍጆታ ተርፎ ምርታቸውን ለሌሎች በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በውጭ ንግድ ሲገነቡ ይስተዋላል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም ከነዚህ ሃገራት ባልተናነሰ መልኩ ለግብርና አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች ቢሆንም የምርት አቅሟ ግን ለአገር ውስጥ ፍጆታም የሚበቃ አልሆነም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን ሳይጨምር ወደ 123 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውሃ ሃብትና ከ36 ሚሊየን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡  እነዚህ የተፈጥሮ ሃብቶች ሃገሪቱ የምትፈልገውን ሰብል በተለያዩ አካባቢዎች ለማምረት እንድትችል እድል ይፈጥራሉ፡፡ ነገር ግን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በሰብል የለማው የአገሪቱ መሬት 16 ሚሊየን ሄክታር ገደማ ያህል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም በመስኖ ልማት የለማው መሬት 1.1 ሚሊየን ሄክታር ያህሉ  ነው፡፡

ስንዴ በአገራችን ከጤፍ ፣ በቆሎና ማሽላ ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ የሚመረት የሰብል አይነት ሲሆን በስንዴ ምርት የሚለማው መሬትም ወደ 1.8 ሚሊየን ሄክታር ይጠጋል፡፡ ከዚህም የሚገኘው ምርት 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ሲሆን የስንዴ ልማት ምርት መጠኑም በሄክታር 27 ኩንታል ነው፡፡ ይህም በአፍሪካ በስንዴ ምርት ልማት በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ ያደርጋታል፡፡ ሆኖም ግን አገሪቱ ለነዋሪዎችዋ የእለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴን ከውጭ በማስገባት ታቀርባለች፡፡ ይህም ከአገሪቱ አመታዊ የስንዴ ፍጆታ 25 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ሲሆን፣ በአመት ስንዴ ከሌሎች ሃገራት ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በአማካኝ 600 ሚሊየን ዶላር ያህል ነው፡፡ በመሆኑም ሃገራችን ስንዴን ለማምረት የሚበቃ መሬት፣ አፈር፣, ውሃ፣ በቂ አምራች ሃይልና ሌሎችም ለግብርና ልማት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችና ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶች ያላት መሆኑ ስንዴን ወደ አገር ውስጥ በግዥ ለማስገባት የምታወጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ቁጭትን ይፈጥራል፡፡

የአገሪቱ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት እንደሚገባ በተለያዩ መንገዶች በማሳየትና በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የኢፌድሪ የግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ ክልልና ፌደራል የግብርና ተቋማት ጋር በመሆን አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በማስቀረት በራስዋ ማምረት የምትችልበትን ሁኔታ መፍጠርን አላማው አድርጎ ወደ ስራ ገባ፡፡  በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥም ተሳታፊ የሚሆኑ አካላትና ቦታዎች የተለዩ ሲሆን በላይኛውና መካከለኛው አዋሽ ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ እንደ ዱብቲ፣አሚባራ፣ገዋኔ፣ፈንታሌና ቲቢላ ያሉ ቆላማ አካባቢዎች በኦሞ ወንዝ አርባ ምንጭ ዙሪያ የሚገኙ ቦታዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ጎዴና አካባቢው ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም እነዚህን ተግባራት ከተለያዩ የፌደራልና የክልል የግብርና ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለማከናወን  እቅድ በመንደፍ የጋራ ግንዛቤ መፍጠሪያ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ የመስኖ ስንዴ ልማትን በቆላማ የአገራችን አካባቢዎች ማስተዋወቅና የአመራረት ስርዓትን በመዘርጋት የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በአዋሽ፣ ኦሞና ሸበሌ ተፋሰሶች ውስጥ የሚገኙና በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ በአርሶ አደር፣ በግል ባለሃብትና በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ እርሻ መሬቶችን የመለየት፣ በተለዩት መሬቶች ላይ ያለውን የመስኖ መሰረተ ልማቶች የውሃ አቅርቦት ሁኔታ፣ አየር ንብረት፣ የአፈር አይነትና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ለመለየት ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በዚህም ለአገር ውስጥ ፍጆታ በቂ የሆነ የስንዴ ምርት ለማምረትና ከዚያም ባለፈ ለውጭ ንግድ ለማዋል የሚያስችሉ አማራጮች ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የስንዴ ምርት ማምረት የሚቻልባቸውን ቦታዎች በመለየትና በምርት ያልተሸፈኑ ቦታዎችን በመስኖ በማልማት እንዲመረትባቸው ማድረግ ዋነኛው ሲሆን ምርቱም ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዙ የተሻሻሉ የስንዴ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ እንዲሁም ሙሉ የአመራረትና እንክብካቤ ሂደታቸውን መከተታተል ዋነኞቹ አማራጮች ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም አሲዳማ መሬቶችን በማከም አንዲሁም ውሃማ መሬቶችን በማጠንፈፍ ወደ ስነዴ ማሳነት ለመቀየር የሚያስችሉ መሬቶችን መጠቀም ነው፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ካሳለፍነው አመት ጀምሮ በዋናነት በአዋሽ ተፋሰስ ዙሪያ ባሉ ቆላማ አካባቢዎች የመስራቱን ሃላፊነት ተረክቦ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ተቋሙ በምርምር ያወጣቸውን ለቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑና የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን ወደነዚህ አካባቢዎች በመውሰድና በማላመድ እንዲሁም በማስተዋወቅ ፍላጎት አንዲፈጠር ማድረግ የቻለ ሲሆን በአፋር ዱብቲ ወረዳ 667 ሄክተር፣ በአሚባራ 1383 ሄክታር፣ በገዋኔ 250 ሄክታር፣ በፈንታሌ 270 ሄክታር እንዲሁም በቲቢላ ወረዳ 440 ሄክታር መሬትን በስንዴ ሰብል ምርት መሸፈን ተችሏል፡፡ በዚህ መጠነ ሰፊ ስራም በምርት አመቱ በአጠቃላይ 3500 ሄከታር መሬት በስንዴ ልማት መሸፈን የተቻለ ሲሆን በባለሞያዎች በተሰጠ ቅድመ ግምትም ከምርቱ በሄክታር ከ40 እስከ 60 ኩንታል የሚደርስ ምርት ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡

ይህንን ውጤታማ ስራም ለሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባን ስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረትን አላማው ያደረገ ብሄራዊ የመስክ ቀን ከየካቲት 1 እስከ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአሚባራ፣ ዱብቲ፣ቲቢላና ፈንታሌ አካባቢዎች የተካሄደ ሲሆን ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ግብርና ሚኒስቴር፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ት፣ከፌደራልና ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች ከክልል፣ ዞንና ወረዳ ግብርና ቢሮዎች የተውጣጡ ሃላፊዎችና ባለሞያዎች፣አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ  አካባቢዎች አዳዲስና የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ይዞ በመቅረብ የማስተዋወቅና የሲዳማና ጨዋማ አካባቢዎችን ጨምሮ ስንዴን በመስኖ የማልማት ተግባርን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የተገኘውን ውጤትም መሰረት በማድረግ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ማስፋት ስራዎችን በማከናወን የተሻሻሉ የስንዴ ቴክኖሎጂዎችንና አጠቃቀሞችን በሁሉም አገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡