የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢስቲትዩት የ2010 ዓ/ም የምርምር ጉዞ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2010 የበጀት ዓመት በሰብል፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በግብርና ምህንድስና፣ በአየር ንብረት፣ ባዮቴክኖሎጂ፣ በምግብ ሳይንስ፣ በግብርና ኢኮኖሚክስና በቴክኖሎጂ ስርጸት ምርምር ዘርፎች ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም የቴክኖሎጂና መረጃዎች ማመንጨት፣ ማስተዋወቅና ማስፋፋት እንዲሁም የአራቢና መነሻ ዘር ብዜት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህም የምርምር ሂደት የተገኙ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ፣ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ፣ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት እንዲደርሱ በማድረግ የግብርናውን ዘርፍ እድገት፣ የምግብ ዋስትናን እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል፡፡ 

ኢንስቲትዩቱ በስሩ ካሉ 17 የምርምር ማዕከላት በተጨማሪም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከሌሎች ምርምር ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቴክኖሎጂ አቅርቦት /ማላመድና ማፍለቅ/፣ ብዜትና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ምርምሮችን የማስተባበርና ድጋፍ የመስጠት ስራዎችን አከናውኗል፡፡ 

በዚህም የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚረዱ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃነት ግብዓት የሚውሉ፣ የውጭ ምንዛሬን የሚያሳድጉና ለዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት የሚረዱ የሰብል፣ የእንሰሳትና የተፈጥሮ ሃብት የምርምር ውጤቶችን ማውጣት ችሏል፡: በተጠናቀቀው 2010 በጀት ዓመት ኢንስቲትዩቱ በድምሩ 114 ቴክኖሎጂዎችንና 339 መረጃዎችን ለማቅረብ ችሏል፡፡ ከሰብል ዝርያ አቅርቦት አኳያ ሲታይ በበጀት ዓመቱ ኢንስቲትዩቱ 42 የሰብል ቴክኖሎጂዎችንና 112 መረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ በሩዝ፣ የማካሮኒና የዳቦ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ማሽላ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም፣የምግብና ብቅል ገብስ፣ ባቄላና ሌሎችም ሰብሎች ዙሪያ የተገኙ ውጤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የቀረቡት ዝርያዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዝርያዎች የምርት ልዩነት ያላቸው ሲሆን ድርቅ፣ ተባይ፣ በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ 

በእንሰሳት ምርምር ዘርፍም 21 ቴክኖሎጂዎችና 62 መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የበግ የፍየል የግመልና የጋማ ከብት ምርትና ምርታማነትና ጥራትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች የሚገኙበት ሲሆን የአገሪቱን የስጋ ምርት በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ለማሳደግ የሚረዱ ናቸው፡፡ የዓሳ ግብርናን ሊያሳድጉ የሚችሉና የተፈጥሮ የውሃ አካላትና ትላልቅ ግድቦችን በመጠቀም ዓሳን በዘላቂነት ለማምረት የሚረዱ 11 መረጃዎች በምርምር የፈለቁ ሲሆን እነዚህም የዓሣ ተረፈ ምርት ብክነትን የሚቀንሱና የዓሣ መኖዎችን ለማዘጋጀት እንዲሁም የዓሣግብርናምርትናምርታማነትንበማሳደግየምግብዋስትናንለማረጋገጥናየአግሮኢንዱስትሪውንግብዓትለማሰደግአስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይም ኢንስቲትዩቱ ሶስት የንብ መኖ ቴክኖሎጂን በማውጣት የንብ መኖ መጠንን ማሻሻል የሚያስችል ስራ ሰርቷል፡፡ 

በሌላ በኩል በበጀት አመቱ 84,124 የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችን በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ቅድመ ማስፋፋት ስራዎች አንዲሳተፉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ለ 43,234 የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችም በዚሁ ዙሪያ የክህሎትና አቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተችሏል፡፡ እንዲሁም በመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት በዓመቱ በሰብል ምርምር፣ በእንሰሳት ምርምር፣ በመሬትና ውሃ ሃብት ምርምር፣ በግብርና ሜካናይዜሽን ምርምርና በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር መስክ የቴክኖሎጂ ብዜት አቅርቦት ስራዎች በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ 

ኢንስቲትዩቱ ከተልዕኮው መነሻነት በስሩ ካሉ የምርምር ማዕከላት እንዲሁምበትብብርሰባት የክልልግብርናምርምርተቋማትናከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነት በምርምር የወጡ ቴክኖሎጂዎችን በተለያየ መንገድ ለተጠቃሚው ለማድረስ ቴክኖሎጂዎቹን የማስተዋወቅና ፍላጎት የመፍጠር ተግባርን የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን ፍላጎት የተፈጠረባቸውንና ተቀባይነት ያገኙትን ቴክኖሎጂዎች መነሻ ዘር ብዜት በማከናወን ለቴክኖሎጂ አባዥ ተቋማትና ተጠቃሚዎች እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ በምርምር ማዕከላት በ681 ሄ/ር ማሳ ላይ በሰብል የአዝርዕት፣ ጥራጥሬ፣ አትክልት፣ ቅባት እህሎች፣ ስራስር፣ ቡናና ቅመማ ቅመም ዝርያዎችን 11,504 ኩንታል የአራቢ፣ ቅድመ መስራችና መስራች ዘሮች፣ 144,800 የሰብል ችግኞች እና 175,000 ቁርጥራጮች መባዛት የተቻለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በ17 የተለያዩ የመዓዛማ ሰብሎች 319,800 ችግኞችና ቁርጥራጮች ማባዛት ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል በእንሰሳት ቴክኖሎጂ ብዜት 37 ኮርማዎች፣ 115 ጊደሮች፣ 231 በግና ፍየሎች፣ 849.750 የዓሳ ጫጩቶች፣ 16,500 የሐር ትል እንቁላሎች፣ 295 የንብ ቴክኖሎጂዎች፣ 251540 ጫጩት ዶሮዎች፣ 180,000 የንብ መኖ ችግኞች፣ እንዲሁም በ26.67 ሄ/ር መሬት ላይ 201 ኩ.ል 20 የሚሆኑ የመኖ ሰብል አራቢ፣ ቅድመ መስራችና መስራች ዘሮች ተባዝተዋል፡፡ 

በተፈጥሮ ሀብት 7,752 ህያው ማዳበሪያ፣ የማባዣ ሳጥንና የቀዝል ትል ቴክኖሎጂዎች ማባዛት የተቻለ ሲሆን፣ በግብርና ምህንድስና የቅድመ ምርት፣ የምርትና የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በባዮቴክኖሎጂ ቲሹ ካልቸር ዘዴን በመጠቀም የተለያዩ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመም ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በቀጣይም የተባዙትን የቴክኖሎጂ መነሻ ዘሮች ለተጠቃሚዎችና አባዥ ተቋማት የማድረስ ስራ ይከናወናል፡፡ 

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስተው የነበሩ የሰብል በሽታዎች መነሻነትም በበጀት ዓመቱ በፀረ ተባይ ላይ በተደረገ ሙከራ በርካታ መረጃዎች የወጡ ሲሆን የበቆሎ ግንደ ቆርቁርንና የአሜሪካ ተምችን፣ የጎመን ክሽክሽን፣ የአፍሪካ ጓይ ትልን በጥጥና በቃሪያ ላይ፣ የቡና ላይ ቅጠለ ሰፊ የሳር አረሞችን፣ የጥጥ ክሽክሽን፣ የስንዴ ሳር አረሞችን፣ቲማቲም የሻጋታ በሽታን፣ የጤፍ ቅጠለ ሰፊ አረሞችን፣ የሽንኩርት ተባይን፣የድንች በሽታንና ሌሎችም በሽታዎችን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ 

የምርምር መገልገያ ግብዓት አቅርቦት ውስንነት በበጀት አመቱ ከታቀዱ የቴክኖሎጂና መረጃ ውጤቶች አፈፃፀም ላይ እንደ ዋነኛ ችግር ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ 

በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አመታት ተጀምረው በሂደት ላይ ያሉና በአዲሱ በጀት አመት ለማከናወን ታቅደው ወደ ትግበራ የተገቡ የምርምር ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት በማሻሻል ተጠቃሚነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡