የምርምር ዳይሬክተሮች ቡድን መስኖን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ምክክርና የመስክ ምልከታ አካሄደ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተመራ 11 አባላት የያዘ የምርምር ቡድን መስኖን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂ ማላመድና ሽግግር ፕሮግራም ላይ ከየካቲት 8-12/2009 ዓ.ም. ምክክርና የመስክ ምልከታበኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አካሄደ፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዓላማ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለምግብ ዋስትና፣ ለእንስሳት መኖና ለወጪ ገበያ የግብርና ምርቶች ለማምረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እና  የመጠቀም አቅምን ለማጎልበት ከሚመለከታቸው የክልሉ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት  ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተከታታይ የድርቅ ክስተቶች ተጋልጦ የቆየ አካባቢ በመሆኑ ይህንን በመቋቋም  ትርፍ አምራች ለመሆን የሚያበቃ ሰፊ መሬትናየውሃ ምንጮች ያለው ክልል ነው፡፡ በተለይም አሁን በክልሉ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የውሃ ግድብ ስራዎች፣ የመስኖ መሰረተ ልማትና የመንገድ ሥራዎች በክልሉየግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሰፋ ለማስረፅና ለማላመድ  መልካም አጋጣሚ መሆናቸው ተገልጧል፡፡ 

ፕሮግራሙ በመኖ እጥረት የሚከሰት ከፍተኛ የእንሰሳት እልቂትን በማስቀረት፣ የክልሉን መንግስት መኖ የማሰባሰብና ማጓጓዝ ጫናና ከፍተኛ ወጪ እንዲቀንስ ማድረግ፤በክልሉ የሚታዩ የምግብ ዋስትና ችግሮች እንዲፈቱና ክልሉን ወደ ተሻለ የማምረት አቅም ለማሳደግ በተለይም ለኤክስፖርት ኮሞዲቲዎች ምርት መስፋፋት መነሻ እንደሚሆን ተገልጧል፡፡ 

በፕሮግራሙ የአፈፃፀም አቅጣጫ ሂደት ላይ ውይይትና ምክክር በተደረገበት በዚህ የምክክርና የመስክ ምልከታ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካሎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም እንግዶች ተሣትፈዋል፡፡