የምርምር ማዕከሉ ለቆላማ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን አስተዋወቀ

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የግብርና ቴክኖሎጂ ፣ዕውቀትና መረጃ ተጠቃሚ በማድረግ በኑሮው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ከሚያደርገው ጥረት አንዱ የእንስሳት መኖና የተፈጥሮ ግጦሽ የምርምር ስራ ነው፡፡ ማዕከሉ በእስካሁን ቆይታው ከ90 በላይ የሰብል፣ ከ50 በላይ የአፈርና ዉኃ እና ከ20 በላይ የእንስሳት ቴክኖሎጂዎች መረጃዎችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ከማድረግም አልፎ ለፖሊሲ አውጭዎች ከፍተኛ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችንና ዕውቀቶችን አፍልቋል፡፡ 

ማዕከሉ የካቲት 18-19 ቀን 2009 ዓ/ም በአሚባራና ገዋኔ ወረዳዎች እያከናወናቸው የሚገኙ የእንስሳት መኖ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ሥራዎችን በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ውስጥ የታቀፉ አርብቶ አደሮችን፣ ከፊል አርብቶ አደሮችን፣ የግብርና ባለሙያዎችንና የተለያዩ  የልማት አካላትን ባሳተፈ የመስክ ቀን በዓል አስጎብኝቷል፡፡ 

የምርምር ማዕከሉ ለቆላማ አካባቢ የሚሆኑና በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ በተለይም ለወተትና ለሥጋ ከብቶች ተስማሚ የሆኑ አራት የመኖ ዝርያዎችን በአሁኑ ወቅት እያባዛ የሚገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህ ዝርያዎች መካከል አልፋ አልፋ /የመኖዎች ንጉስ/ በመባል የሚታወቀው ዝርያ ይገኝበታል፡፡ ዝርያው ለወተት ከብትና ለዶሮ እርባታ ተስማሚና ምርታማነትን የሚያሳድግና ዕድገቱም ፈጣን በመሆኑ በቆላማ አካባቢዎች ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምርምር ማዕከሉ ያወጣቸውን የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን ባለው ውስን መሬት ላይ በማባዛትና ከሚመለከታቸው የክልሉ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ለእንስሳት እርባታ ትልቅ ማነቆ የሆነውን የመኖ እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን በወቅቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች የዘር እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍም ዘር የማሰራጨት ሥራ በእነዚህ ክልሎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡