በማህበር የተደራጁ የፈንታሌ ወረዳ አርብቶ አደሮች የዶሮ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን ከማፍለቅ ኃላፊነቱ ጎን ለጎን ለውጥ አምጪ የሆኑ ለቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋትና የማስተዋወቅ እንቅስቃሴ በሰፊው እየሠራ ይገኛል፡፡

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከሚያስፋፋቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል በምርምር የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ በአፋር ክልል ከመካከለኛው እስከታችኛው አዋሽ ድረስ ለሚኖሩ ከፊል አርብቶ አደሮች ከክልሉ አርብቶ አደር ግብርና ቢሮና ከሚመለከታቸው የወረዳ አርብቶ አደር ግብርና ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት ለአካበቢው ተስማሚ የሆኑ የበግና የፍየል ዝርያቸው በብዛት እንዲዋለዱ በማድረግ የማሰራጨት ሥራም እየሠራ ይገኛል - ማዕከሉ፡፡ 

ከዚሁ ጎን ለጎን ለአፋር አካባቢ ተስማሚ የሆኑና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ የዶሮ ዝርያዎች በአሁኑ ወቅት በአሚባራ ወረዳ በተቋቋሙት የሠፈራ ጣቢያዎች ለተሰባሰቡ ከፊል አርብቶ አደሮች ተሰራጭተው ተጠቃሚ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በምሥራቅ ሸዋ ዞን በፈንታሌ ወረዳ የምርምር ማዕከሉ በማህበር ለተደራጁ የቤት እመቤቶች የዶሮ ዝርያዎቹን በማስተዋወቅና ድጋፍ በማድረግ በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንዲያመጡ መሠራቱን በማዕከሉ የእንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ መገርሣ ገልፀዋል፡፡ 

ወ/ሮ አሚና አህመድ በምሥራቅ ሸዋ ዞን የፈንታሌ ወረዳ ሳራ ዌይባ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የስምንት ልጆች እናት ናቸው፡፡ በቀበሌያቸው የኡርጂ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ሲሆኑ ከምርምር ማዕከሉ ጋር ከተገናኙ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ማዕከሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴ ቴክኖሎጂ የሰጣቸው መሆኑን ገልፀው በአሁን  ወቅት ለማህበራቸው የ300 ዶሮዎች ድጋፍ አድርጎላቸው ሁሉንም የማህበሩን አባላት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ አሚና አያይዘውም የተደረገላቸው ድጋፍ በኑሯቸው ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑንና የምርምር ማዕከሉ የሚያደርግላቸው ድጋፍ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡