የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለሁለት ተመራማሪዎች የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጠ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአገራችንን የግብርና ዘርፍ ዕድገት የተለያዩ ችግር ፈች የሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀትን በማመንጨትና በማቅረብ ለአገራዊ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማደግ፣ ለአርሶና አርብቶና አደሩ የገቢ ምንጭ ማደግና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ የተጫወተና እየተጫወተ የሚገኝ ስኬታማ አገራዊ ተቋም ነው፡፡ ለዚህ የተቋሙ የስኬት አስተዋጽዖ ምክንያት ከሆኑ ዓበይት ምክንያቶች መካከልም የተመራማሪዎች ያልተቆጠበ ሙያዊ አስተዋጽዖና ቁርጠኝነት አንዱ ነው፡፡

በአገር ደረጃ ለተቀመጡ የግብርናው ዘርፍ ግቦች መሣካት የግብርና ምርምርን አስተዋጽዖ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርምሩን ውጤታማ ለማድረግ የምርምር አቅም ግንባታ በምርምር ቁሳቁስ፣ በምርምር ሰው ኃይል፣ በምርምር መሰረተ ልማት በመካከለኛ ገቢ የሚገኙ ሌሎች አገራት የደረሱበት ተርታ መድረስ ልናሳካው ለምንገፈልገው አገራዊ ግብ እውን መሆን መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በምርምር ሰው ኃይል በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸውንና ዛሬ ለደረስንበት የግብርና ዕድገት ውጤት ዕድሜያቸውን ሰውተው ያለተቆጠበ አስተዋጽዖ ሲያደርጉ ለቆዩና እያደረጉ የሚገኙ አንጋፋ ተመራማሪዎቻችንን ለነዚህ ግቦች መሳካት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ የግንባር ቀደም መሪነት ማሰቀመጡ ለተመራማሪዎቻችን ክብርም ሆነ ለወደፊት ላስቀመጥናቸው አገራዊ ግቦች መሳካት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡ 

በመሆኑም የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ በተቋም ደረጃም ሆነ በአገራዊ ምርምር ሥርዓቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በማገልገል ለቴክሎጂያዊ ትሩፋቶቻችን መገኘት ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትንና ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያላቸውን ተመራማሪዎች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ እና ላሳዩት ግንባር ቀደምነት ዕውቅና በመስጠት በምርምር ሥርዓቱ ጠብቆ የማቆየትና ክህሎታቸውንና ልምዳቸውን በተገቢው ደረጃ ለተተኪ ተመራማሪዎች ለማስተላለፍ የሚችሉበት ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ አኳያ በተቋሙ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉና በግብርና ምርምር ዘርፍ የመጨረሻ የእድገት መሰላል ላይ የሚገኘውን የመሪ ተመራማሪ ደረጃ  መሥፈርቶች በብቃት ያሟሉ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ የምርምር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት 2009 / ሲሆን የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ 

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተቋሙን ለረጅም ዓመታት በሙያቸው ሲያገለግሉ ለቆዩና በማገልገል ላይ ለሚገኙ ሁለት አንጋፋ ተመራማሪዎች የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡ ዕወቅናው በተቋም ደረጃም ሆነ በአገራዊ ምርምር ሥርዓቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በማገልገል በአገር ደረጃ ጥቅም ላይ ለዋሉ የግብርና ቴክሎጂ ትሩፋቶች መገኘት ጉልህ አስተዋጽዖ ላደረጉትና ሰፊ ተሞክሮና ክህሎት ላላቸው ለእነዚህ ተመራማሪዎች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖና ላሳዩት ግንባር ቀደም የመሪነት ሚና ዕውቅና በመስጠት በምርምር ሥርዓቱ ጠብቆ ማቆየትንና ክህሎታቸውንና ልምዳቸውን በተገቢው ደረጃ ለተተኪ ተመራማሪዎች ለማስተላለፍ የሚችሉበትን ሥርዓት መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ 

ግንቦት 9 ቀን 2010 / በተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ ዕውቅና የመስጠት ሥነ ሥርዓት ላይ ኢንስቲትዩቱን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉና ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለምርምሩ ዘርፍ መጎልበት ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የተነገረላቸው / ጌታቸው አገኘሁ ጀንበሩ እና / ቶለሣ ደበሌ ዲሌሳ በአገሪቱ የግብርና ምርምር ሥርዓት ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጠውን የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ 

የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ በተመራማሪዎች የዕድገት መሠላል ከከፍተኛ ተመራማሪ ቀጥሎ የሚሰጥ የመጨረሻው ትልቅ ደረጃ ሲሆን፤ ተመራማሪዎች በምርምር ሥርዓቱ ያበረከቷቸው ውጤቶች፣ ለህትመት ያበቋቸው ጽሑፎች፣ ማህበረሰቦችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግና በማህበረሰብ አቅም ግንባታ ረገድ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች እንዲሁም በምርምር ሥርዓቱ ውስጥ በምርምር ሥራ አመራር የነበራቸው ድርሻ ተገምግሞ የሚሰጥ ነው፡፡ 

መሪ ተመራማሪ / ጌታቸው አገኘሁ 1991 ጀምሮ በተፈጥሮ ኃብት ምርምር በአፈር ልማት የምርር ዘርፍ በተለይም በተቀናጀ የአፈር ለምነትና በአግሮኖሚ ምርምር የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በማውጣትና ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በርካታ ሠረራዎችን አከናውነዋል፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 2006 / 5ኛው አገር አቀፍ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዕውቅና እና የሜዳሊያ ሽልማት ላይም በብቅል ገብስ ምርምር ዘርፍ እውቅናና የሜዳሊያ ሽልማት ከባልደረቦቻቸው ጋር አግኝተዋል፡፡ ከግልና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር 29 በላይ የጆርናል ጽሑፎችና 36 የተለያዩ ህትመቶችን፤ በአጠቃላይ 65 ጽሑፎችን ለህትመት በማብቃት ለግብርና ሳይንስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ 

መሪ ተመራማሪ / ቶለሣ ደበሌ 1982 ጀምሮ በአፈርና ውሃ ምርምር በአፈር ለምነትና በአሲዳማ አፈሮች ማሻሻያ የምርምር ዘርፍ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የኮምፖስትና የቨርሚ ኮምፖስት ቴክኖሎጂዎችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በማውጣት፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመንደፍና በመተግበር፣ ለተፈጥሮ ኃብት ምርምር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉና መረጃ የሚሰጡ የግብርና ልማት ችግሮችን በመለየት፣ የቴክኖሎጂ ስርጸትና ተቀባይነት ሥራዎችን በመተግበር፣ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በማውጣትና ለተጠቀሚዎች በማስረስ ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡  

በተጨማሪም 58 ጽሑፎችን በማሳተም ለግብርና ሳይነስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ በምርምር ሥርዓቱ ያበረከቷቸውን ውጤቶች፣ ለህትመት ያበቋቸውን ጽሑፎች፣ ማህበረሰቦችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ባደረጉባቸው ሥራዎች፣ በማህበረሰብ አቅም ግንባታ የሠሯቸውን ሥራዎች፣ ለምርምር ሥርዓቱ ያበረከቷቸውን የምርምር ሥራ አመራር አስተዋጽዖዎች እንዲሁም በምርምር ሥርዓቱ ያላቸውን ተቀባይነትና ሥነ-ምግባር በመስፈርትነት በመጠቀም የሚሰጥ ማዕረግ ነው፡፡