COVID-19 Response
 

ለአረንጓዴ አሻራ የፍራፍሬ ዛፍ ችግኝ ተከላ

የደን ሽፋን በኢትዮጵያ በቁጥር ጣራ ስር ሊሆን እንደማይችል ምሁራኑ ይናገራሉ፤ እንዲሁም በቀደሙት ጊዜያት በአገሪቱ ደን በዘመቻ እንደሚተከል ታሪካዊ ዳራዎች ሲያስረዱ የአገሪቱ የደን ሽፋንም 4ዐ በመቶ እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የደን ሽፋንን በኢትዮጵያ ለማሣደግ በእያመቱ 2ዐ ሄክታር መሬት ያክል በደን ለመሸፈን ታቅዶ የዛፍ ችግኞችን በዘመቻ በመትከል ሁለተኛው ዓመት ላይ እንደምንገኝ ይታወሣል፡፡ በያዝነው ዓመትም በአረንጓዴ ሽፋን መርሀ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኝ ሊተከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዋናው መ/ቤት የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ ሐምሌ 14 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም. በመልካሣ የግብርና ምርምር ማዕከል የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡ የችግኝ ተከላውን ከሌሎች የዛፍ ችግኝ ተከላዎች ለየት የሚያደርገው የምርምር ማዕከሉ ያዘጋጃቸው ችግኞች የፍራፍሬ ችግኞች ሲሆኑ እንዲተከል የታቀደውም አስተማማኝ ጥበቃ በሚደረግለት በማዕከሉ ጊቢ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ዶ/ር በድሩ በሽር የመልካሣ የግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አቅርበዋል፡፡ ቀጥለውም ማዕከሉ በዋናነት የፍራፍሬ ሰብልን በማስተባበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለአረንጓዴ አሻራ የኩላችንን አስተዋፅዖ ለማድርግ በዚህ ዓመት የፍራፍሬ ችግኞችን በማዕክሉ ጊቢ ውስጥ በዘመቻ እንዲተከሉ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ፈቶ ኢሴሞ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በአገሪቱ ታቅዶ እየተሠራ ያለውን የደን ሽፋን ለማሣደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የተቋሙ አሻራ እንዲሁም ተሣታፊነት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀው የፍራፍሬ ችግኝ መትከሉ ደግሞ ለምግብነት ከሚውለው ፍጆታ አንፃር ሲታይ እጥፍ ድርብ ውጤታማ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ በዋናነት ለምግብ ዛፍ ችግኝ ማፍላት እንዲሁም በፍራፍሬ ችግኝ እና ምርት ማስገኘት መስራት እንዳለበት እንዲሁም ለወጣቶች ስልጠና መስጠት የሚያስችል እቅም እንዲኖረው አሣስበዋል፡፡

ዶ/ር አስማረ ዳኘው በመልካሣ ግብርና ምርምር የሰብል ምርምር የስራ ሂደት ተጠሪ እንዳስረዱት የተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች ከማንጎ ሁለት ዝርያዎች እንዲሁም ከአቮካዶ ሶስት ዝርያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ እነሱም፡ ከማንጎ አፕል ማንጎ እና ቶሚ አትኪንስ የሚባሉ ዝርያዎች ሲሆኑ ከአቮካዶ ደግሞ ሐስ፣ ፉርቴ እና ኤቲንገር የሚባሉ ዝርያዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ዝርያዎቹ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውሉት የፍራፍሬ ዛፎችን በቴክኖሎጂ ለማባዛት እንደ እናት ዛፍ ለመጠቀም ነው ብለዋል፡