As a national research institute, EIAR aspires to see improved livelihood of all Ethiopians engaged in agriculture, agro-pastoralism, and pastoralism through market-competitive agricultural technologies.

Latest News

EIAR IN THE MEDIA


 

የግብርና ትምህርት ምርምርና ኤክስቴንሽን ጥምረት ለውጤታማ የቴክኖሎጂ ማፍለቅና ሽግግር ሂደት በሚል ርዕስ የአንድ ቀን አውደጥናት ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን የአውደ ጥናቱ አላማም በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የግብርና ምርምር፣የትምህርትና የኢክስቴንሽን ተቋማትን በማጣመር  ከዘርፉ የሚገኙ ውጤቶችን ማሳደግ የሚል ነው፡፡

ክቡር ዶ/ር እያሱ አብርሃ የግብርና ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ በአውደ ጥናቱ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ወቅት እንደገለፁት ግብርናው በተለያዩ ጊዜያት እያደገና እየተለወጠ የሚገኝ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል መዋቅራዊ ለውጥ ባለመምጣቱ ምክንያት የውጭ ንግድና አግሮ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳካት አልተቻለም ያሉ ሲሆን በየአመቱ እየተመዘገበ ያለው የምርት መጠን ጥሩ ቢሆንም በቴክኖሎጂ ስርጭት ዙሪያ የሚቀረው ነገር እንዳለ ገልፀዋል፡፡

ቴክኖሎጂ ከምርምር ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲዎችና ከተጠቃሚዎች ሊገኝ የሚችል እንደሆነ የገለፁት መኒስቴር ድኤታውየዚህ የቅንጅት ስራ አስፈላጊነትም ይህንን ወደተግባር ለመቀየር ነው ብለዋል፡፡ በሰው ሃይል፣ በመሰረተ ልማትና በበበጀት ተቋማዊ አቅምን መገንባት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያሰለጥኗቸው የግብርና ባለሞያዎች ብቃትን ማሳደግ ለቴክኖሎጂዎች ስርጭትና ተደራሽነት ወሳኝና ችግር ፈቺ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የምርምር ተቋማትን፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የግብርና ኤክስቴንሽን ተቋማትን በማቀናጀት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት የመንግስት ድርሻ ይሆናል ብለዋል፡፡ ይህ ጥምረትም ተግባር ተኮር እንዲሆንና ከቴክኖሎጂ የማላመድና የማመንጨት ሂደቱ የሚገኘው ውጤትም ለተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርስ የማድረጉ ሂደት በተጠናከረ ሁኔታ ተጀምሯል ያሉ ሲሆን፣ ይህም በሃላፊነትና  በተጠያቂነት የሚታገዘ ሲሆን በዚህ ዙሪያም መንግስት በአመራርም ሆነ በበጀት ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ባለፉት 8 ዓመታት አርሶና አርብቶ አደሩን፣ተጠቃሚውንና ባለሞያዎችን አሳታፊ በማድረግ በግብርና ኤክስቴንሽን ዙሪያ የተከናወኑ ምርጥ ተሞክሮዎችን የማስፋት ስራና  ያስገኘውን ውጤት ለመለየት  ጥናት የተካሄደ ሲሆን ከጥናቱ የተገኙ ውጤቶችም በዚሁ አውደ ጥናት ላይ ቀርበዋል፡፡ ከዚህ መነሻነትም በግብርና ምርምር በተለይም በቴክኖሎጂ ማፍለቅና ማስረፅ ስራ ላይ ያሉትን ውስንነቶች በመፈተሽ በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የተጠቃሚውን አቅም ከመገንባት አኳያ እንዲሁም በምርምር የሚወጡ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ከአካባቢ ስነምህዳር እንዲሁም ሶሾኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ወደተጠቃሚዎች ማድረስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችና በዚሁ ዙሪያ የግብርና ኤክስቴንሽን ያስገኘው ፋይዳ ውስንነት በማንሳት ፈጣንና ዘላቂነት ያለው የግብርና እድገት ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂዎች በተፈለገው ጥራትና መጠን ማፍለቅ ብሎም ወደተጠቃሚ አርሶና አርብቶ አደሮች ማድረስ በትኩረት በማድረግ የግብርና ኤክስቴንሽን ስራ በተጠናከረ ሁኔታ ሊሰራበት እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተገልፃል፡፡

የዚህ መድረክ አላማ በጥናቱ ወቅት የታዩ ክፍተቶችን ለመተንተንና  ወደፊትስ ምን መደረግ ይኖርበታል በሚሉ ርዕሶች  ዙሪያ ያለንን እውቀት ልምድና አቅም በጋራ በማዋሃድ ሃሳቦችን ለመለዋወጥ እንዲሁም ይህንን ወደ ተግባር በመቀየርም የሚታይ ውጤት ላይ ለመድረስ መሆኑን  የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ  ጥናቱን መሰረት በማድረግ Gaps In Methods and Linkages in Ethiopian Agricultural Research and Extension በሚል ርዕስ ባቀረቡት ፅሁፍ ላይ የገለፁ ሲሆን፣ ከዚህ ውይይት የሚገኘውን ግብዓት መነሻ በማድረግም የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኤክስቴንሽን ቢሮዎች እንዲሁም  ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የየድርሻቸውን  ሃላፊነት በመውሰድ ወደ ስራ እንዲገቡና የታዩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቅንጅት ለመፍታት አይነተኛ መፍትሄ ነው ሲሉ ይህንንም ጥምረት በውል ስምምነት በማሰር ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን  መለየት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ተጠቃሚነት በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ የመጣ ሲሆን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ፍላጎቱን ለመጨመርም የተለያዩ አመቺ ዘዴዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ድሪባ ገለቲ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የምርምር፣የኤክስቴንሽንና የትምህርት ተቋማት እርስ በርስ መማማርና በጋራ መስራት ለአገሪቱ ግብርና እድገት ወሳኝ ነው ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ አካላት በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን አቅምም በገለፃቸው ወቅት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ምክትል ዳይሬክተሩ Rationalizing The Need For Enhanced Linkage በሚል ርዕስ የአገሪቱን የግብርና እድገት ጉዞና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ከተለያዩ ጥናቶችና መረጃዎች መነሻነት ያቀረቡ ሲሆን በዘርፉ የተሻለ እድገት ለማምጣት በቅንጅት መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

የምርምር ስራዎች ለግብርናው ዘርፍ እድገት ከሚኖራቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ አንፃር የተሰጠው ትኩረት በቂ ነው የሚባል ባይሆንም ምርምር ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ  በአመራር፣ በሰው ሃይል፣ በበጀት፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎችም አቅርቦቶች ላይ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ በአውደ ጥናቱ ወቅት የተገለፀ ሲሆን በዚህ አውደ ጥናት ላይ ተሳታፊ የሆኑት በአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው አካላት እንደመሆናቸው መጠን በጋራ በመመካከርና በማቀድ ውጤቶችን በመገምገምና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማሳደግ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከካስኬፕ የግብርና ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚሁ አውደ ጥናት ላይ በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዲኖች፣ የፌደራልና የክልል ምርምር ኢንስቲትዩት ሃላፊዎችና የኤክስቴንሽን ሃላፈዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የካስኬፕ ፕሮጀክት በኔዘርላንድስ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ከግብርና እድገት ፕሮግራም ኤ.ጂ.ፒ ጋር በጋራ በመሆን በአገሪቱ አራት ዋና ዋና ክልሎች ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ ከግብርና ቢሮዎች፣ ከግብርና ኤክስቴንሽን መምሪያዎች፣ ከ5 የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከዋጊኒገን ዩኒቨረሲቲ ጋር በመቀናጀት በምርጥ ተሞክሮ ማስፋፋትና በተሻሻሉ የምርምር ዘዴዎች ማስፋፋት ስራ ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡

 

 

Upcoming Events

Research Areas

Research Centers