የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቋሚነት ለቀጠራቸው አዳዲስ ሰራተኞች በተቋሙ ህጎች ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ስልቶች ዙሪያ ከመጋቢት 18 እስከ 20 ቀን 2009 ዓ.ም የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሰጠ፡፡

በለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት የተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ዋነኛ አላማ የተቋሙን የውስጥ የአሰራር ስርዓቶች፣ በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ፣  የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የሥነ ምግባር መርሆዎች፣  የግዢ፤ የፋይናንስና የንብረት አጠቃቀምና አያያዝና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ተቋሙን ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በቋሚነት የተቀላቀሉ ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማስቻል በተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታ የውስጥ አሰራሮችንና ህገ ደንቦችን ተከትሎ በመስራት የተቋሙን ራዕይ የሚያሳካ ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን የገለፁት የኢንስቲትዩቱ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በተቋሙ የውስጥ አሰራር ስርዓት ዙሪያ በቂ ግንዛቤና መረጃ ካለመኖር በመነጨ የሚከሰቱ የህግና ደንብ ጥሰቶችን ከወዲሁ ለመከላከልና ተከሰተው ቢገኙ በምን መልኩ መፍታት እንደሚቻል ለማመላከት የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተቋሙን መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ (ቢ.ፒ.አር) እንዲሁም ሚዛናዊ ስኮር ካርድ (ቢ.እስ.ሲ)፣የተቋሙን የለውጥ ሠራዊት ግንባታና የዜጎች ቻርተር አፈጻጸም፣ በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በተቋሙ የሰው ኃይል አስተዳደርና የስልጠና መመሪያዎች፣ በተቋሙ የሠራተኛ ዲሲፕሊንና ተያያዥ ሕጎች፣ ደምቦችና መመሪያዎች፣ የተቋሙ ሠራተኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ ምግባር መርሆዎችና ሙስናን የመከላከል ዘዴዎች እንዲሁም በተቋሙ የግዢ፤ የፋይናንስና የንብረት አጠቃቀምና አያያዝ መመሪያዎች ዙሪያ በሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን በፅሁፎቹ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በዋናው መስሪያ ቤት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አዳዲስ ሰራተኞች በተጨማሪ ከተቋሙ ማዕከላት የተመረጡ ተወካዮችም ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን፣ ተወካዮቹ ከስልጠናው የቀሰሙትን ግንዛቤ በመውሰድና በየማዕከላቱ መድረክ በመፍጠር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለተቀጠሩ ሰራተኞች እንዲያከፍሉ ይደረጋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሙ አካል የሆነው የጉብኝት ፕሮግራም በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል ተካሂዷል፡፡ ዶ/ር ክበበው አሰፋ ብሄራዊ የጤፍ ምርምር አስተባባሪና የጤፍ ተመራማሪ ጉብኝቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት ሲሆን፣ የማዕከሉን ምስረታ ያለፈባቸውን ሂደቶችና አሁን የደረሰበትን ደረጃ የሚያስቃኝ ፅሁፍ ለጎብኚዎች አቅርበዋል፡፡ ማዕከሉ በእንሰሳት ምርምር ዙሪያ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትንና  በዚህ አመት በዝርያ አፅደቂ ኮሚቴ አፀድቆ ያወጣቸውን ዝርያዎችም ተጎብኝተዋል፡፡ በመጨረሻም በግንዛቤ ማስጨበጫና የጉብኝት ፕሮግራሙ ዙሪያ አጠቃላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡