COVID-19 Response
 

ቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በ 50.9 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የምርምር መስኖ መሰረተ ልማት አሰመረቀ

በኢትዩጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ ከሚገኙት ማዕከላት መካከል አሰላ የሚገኘው ቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ሲሆን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍልቅ የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት ለማሻሻል የበኩሉን እየተወጣ የሚገኘ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በአሁን ሰአት የምስራቅ አፍርካ የግብርና ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮጀክት የስንዴ ልህቀት ማዕከል በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የምርምር ተግባሩን ለማሻሻል ይረዳውም ዘንድ ከፍተኛ የምርምር መስኖ መሰረተ ልማት ገንብቶ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግስት  ሀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በማዕከሉ ግቢ እና ከማዕከሉ ጊቢ ውጭ የተገነባውን የመስኖ ውሀ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ አስመርቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ኡመር ሁሴን፤የኢትዩጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈቶ ኢስሞ እና የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች በጋራ ሪቫን የመቁረጥ ስነስርአት ያከናወኑ ሲሆን  የግብርና እድገት ፕሮግራም /AGP 2/   አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሶፊያ ካሳ  የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገውላቸዋል፡፡ የመሰረተ ልማቱ የገንዘብ ድጋፍ ከሁለተኛው የግብርና እድገት ፕሮግራም /AGP 2/ የተገኘ መሆኑንም የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የምርምር መስኖ መሰረተ ልማቱ 50.9 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅም 2 አመታትን ፈጅቷል፡፡ ሌላው ፕሮጀክቱ 4 የውህ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ 111 ሺህ  ሜትሪክ ኪዩብ ውሀ የመያዝ አቅም ያለው እና ከ71 ሄክታር በላይ መሬትን ለማልማት የሚያስችል አቅምም ያለው ነው፡፡

ይህ መሰረተ ልማት ለሌሎች እንደመነሻ ሆኖ እንደሚያገለግልና በተለያዩ ክልሎች ለተጀመሩ ተመሳሳይ የመስኖ  መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማሰልጠኛ እና ሰርቶ ማሳያ ይሆናል ሲሉ ያስረዱት ደግሞ  የፕሮጀክቱ መሀንዲስ እና ቁጥጥር አስተባባሪ በመሆን ሲሰሩ የነበሩት ዶ/ር  ፋንታሁን አበጋዝ ሲሆኑ በተለይ ተመራማሪው የማዳቀል ስራን በአመት አንድ ጊዜ ክረምትን ጠብቆ ይሰራ የነበረውን ምርምር እና አመታትን የሚወስድባቸውን የምርጥ ዘር ማፍለቅ ስራ በግማሽ እንዲቀንስላቸው የሚያደርግ ነው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡መገንባቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና የስራ መነሳሳትንም እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ የቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል  ሰራተኞች  ናቸው፡፡

በምርቃት ስነስርአቱም ላይ በስራው ላይ  ለተሳተፉ ሰራተኞች ፤አስተባባሪዎች እና የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር ሾደብ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽንን ጨምሮ ለስራው የተለያየ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰብና ድርጅቶች ዋንጫ፤ የእውቅና ሰርተፊኬት እና የተለያዩ ስጦታዎች የተበረከተላቸው ሲሆን  ተሸላሚዎችም በእውቅና አሰጣጥ ሂደቱ መደሰታቸውንና የስራ መነሳሳትንም እንደሚፈጥርላቸው አስገንዝበዋል፡፡

 

በመጨረሻም ይህ ትልቅ አቅምን መፍጠር የሚችልና ልምድን በመስጠትም ለሌሎች ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ፕሮጀክት በአስተባባሪና ጥገና ባለሙያ እጥረት ግቡን ሳያሳካ እንዳይቀር የዘርፉ ባለመያውችን አቅም ከመገናባትና ከማሰልጠን ጋር የተገናኙ ስራዎች በጊዜ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ሌላው እንደአብዛኛው የሀገራችን ልምድ ክረምትንና ዝናብን ብቻ ጠብቀን የምንሰራውን የግብርና ስራ በማሻሻል በበጋም ወራት መስኖን ተጠቅመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገራችንን አርሶ አደር ከድህነት የምናወጣበትና የተሸሻሉ አሰራሮችን ለአርሶ አደሩ ከማሳየት አንጻር የመሰረተ ልማቱ ጅምር  ይበል የሚያሰኝ ነውና የሚመለከታቸው አካላት ስራውን ለአርሶ አደሩ ከማድረስና ብሎም ተመራማሪው ደርቦ እንዲሰራ ከማድረግ ይልቅ የራሱ የሆኑ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በቦታው በማስቀመጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡