ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በስኬት አከናወነ
************************************************************
(ኢግምኢ) አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በጋራ በመሆን ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በሀገር ደረጃ ላማሳካት የታቀደውን የአረንጓዴ አሻራ ክንውን እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ተስፋን እንትከል”! በሚል መሪ ቃል በሸገር ከተማ አስተዳደር፤ ገላን ክፍለ ከተማ ሲዳ አዋሽ ወረዳ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬከተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በጥቅሉ የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ለአገራችን ያለው ሚና ፈርጀ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን ለምሳሌ አቮካዶ፤ ሙዝ፤ አፕል፤ ቡና እና የመሳሰሉትን ለመትከል ዝግጅት ጨርሰን መገናኘታችን እጅግ የሚያስደስትና የሚያኮራ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ንጉሴ በተጨማሪም ችግኝ መትከል ብቻም ሳይሆን ተንከባክቦ የማስጸደቁንም ጉዳይ በማሳሰብ ማህበረሰቡ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራውን ለማሳረፍ በነቂስ በመምጣቱ እና በመሳተፉ አመስግነዋል፡፡
አቶ ደረሠ ግርማ የገላን ክፍለ ከተማ ምክትል አስተዳደሪ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ ብሎም ለከተማችን በብዙ መልኩ ጥቅም ያላቸውን ችግኞች ለመትከል መቻሉ በመንግስት የታለመውን ግብ ለማሳካትና ህብረተሰቡንም የሚጠቅም መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ዘገባ፡ አንተነህ ይልማ
ፎቶግራፍ፡ ሰሙንጉስ የማነ