
በኢትዮጵያ ሃይብሪድ የዘር ስርዓት በተለይም በማሽላ የዘር ስርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ፤ የዓለም የምግብ ኖቬል ተሸላሚ የሆኑት ሎሬት ፕ/ር ጋቢሳ ኤጀታ እና ሌሎች የግብርና ዘርፍ አመራሮች እና ሳይንቲስቶች በተገኙበት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሕሩይ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስተላለፍ ስብሰባውን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈቶ ኢስሞ ዘር ለግብርናው ዘርፍ መጎልበት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው ውይይቱም እዚህ ላይ ያተኮረ መሆኑ በቀጣይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በሁነቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ የግብርናውን ዘርፍ ሚና ለማሻገር ይህ መድረክ በጣም ወሳኝ ነው ሲሉ የዘር እሴት ሰንሰለትን በተመለከተ በርካታ ስራ መሰራት ያለበት ሲሆን ለዚህ ደግሞ የምርምር ሚና በተለይ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ፤ በማላመድ እና በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ግርማ በተጨማሪም ፕ/ር ጋቢሳ ኤጀታ በአፍሪካ የሚሊዮኖች አርሶ አደሮችን ህይወት የቀየረ ስራ ሰርተዋል በኢትዮጵያም በዛው ልክ እንዲሆን በቀጣይ ጠንክሮ በመስራቱ ላይ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ለዚህም የዛሬው መድረክ መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉ አበክረው ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም በተለይ በማሽላ ምርምር እና ውጤት የዓለም የምግብ ኖቬል ተሸላሚና እንደዚሁም የሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤት የሆኑት ሎሬት ፕ/ር ጋቢሳ ኤጀታ በንግግራቸው ለግብርናው ዘርፍ መጎልበት የአሜሪካን እና ሌሎች ያደጉ ሃገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት በመስጠት አሰገንዝበዋል፡፡ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር የተናበበ የሰው ሃይልም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሃይብሪድ ዘር ስርዓት በአሜሪካ ከተጀመረ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን አርሶ አደሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ከፔርዱ ዩኒቨርስቲ፣ ከግብርና ምርምር እና ከሌሎች ተቋማት በተውጣጡ ተመራማሪዎች ገለጻ ቀርቦ በወደፊት አቅጣጫ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የእለቱ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
