You are currently viewing “ወንድ ጥጆችን ከማስወገድ …….. እንደ ሀብት ምንጭነት መጠቀም”

“ወንድ ጥጆችን ከማስወገድ …….. እንደ ሀብት ምንጭነት መጠቀም”

  • Post author:
  • Post category:News
  • Post comments:0 Comments
  • Reading time:1 mins read

ሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከል/ግንቦት 6/2ዐ17 ዓ.ም.

“ምርምር ለግብርና ቴክኖሎጂ ሣይንሣዊ ክንዱ ነው”
“ግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ የማይናወጥ ነው”
ፕሮፌሰር ንጉሤ ደቻሳ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ምርምር ማዕከል በምርምር የተደገፈ የማድለብ ቴክኖሎጂ በመቀየስ ወንድ ጥጆች ተወልደው ጡት ከጣሉበት ጊዜ እስከ ሶስት ዓመታት አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉ ጥናት በማድረግ እና በማድለብ በጥናቱ ውጤት መሠረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዘመናዊ አሠራር ዘርግቷል፡፡

ይኸንኑ አስመልክቶ የማዕከሉ የእንስሳት ምርምር ዘርፍ ግንቦት 6 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም. ባደረገው ፕሮግራም 96 የሚደልቡ ኮርማዎችን ለተደራጁ 16 የወጣት እና ሴት አርሶ አደር ማህበራት አስተላልፈዋል፡፡ አስራ ስድስቱ ማህበራት እያንዳንዳቸው ከአምስትና ከዚያም በላይ አባላት ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማዕከል ዳይሬክተሩ ተወካይ ዶ/ር እንዳለ ያዴሣ የእንስሣት ሥነ-ምግብ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በንግግራቸው የማዕከሉ የእንስሳት ምርምር ዘርፍ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ምርምር በማድረግ አዳዲስ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች እንዲሁም ለሌሎች ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ አሁንም ከምዕራብ ሽዋ፣ ከደቡብ ምዕራብ ሽዋ እና ከሸገር ሲቲ ለተደራጁ 16 የወጣትና ሴት አርሶ አደር ማህበራት 96 የተሻሻሉ ኮርማዎችን በማድለብ ስራ ከነሙሉ ፖኬጁ እንደ መነሻነት ሲያበረክቱ ማዕከሉ ባዘጋጀው የሥራ ዕድል ፈጠራ ወጣቶች እና ሴቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር እንዳለ ጨምረውም ማዕከሉ አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት እና ሌሎችንም ጨምሮ ከ4ዐዐ በላይ በሆኑ የምርምር ሙከራዎች የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት ለማህበረሰቡ በማዳረስ ላይ ይገኛል። በእንስሳት ዘርፍ በወተት ከብቶች፣ በእንስሳት መኖና ስነ-ምግብ እንዲሁም በዶሮ ርባታ ከመንግስት ዕቅድ ጋር ተያያዥነት ላለው የሌማት ትሩፋት ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ በንግግራቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሣ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የዕለቱን ዝግጅት እንደ አገር ሁሉም የሚፈልገው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ግብርና ለኢትዮጵያ ሕልውናዋ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ንጉሴ ኢትዮጵያ 18 ዓይነት ሥነ-ምህዳር ያላት የበርካታ ዕፅዋቶች እና አዝርዕት ምንጭ፣ ከፍተኛ የከብት ሀብት እንዲሁም በርካታ የከብት ዝርያዎች ያሏት በግብርና ሀብታም እና በአፍሪካ ቀዳሚ አገር እንደሆነች ገልፀዋል፡፡ “ምርምር ለግብርና ቴክኖሎጂ ሣይንሣዊ ክንዱ ነው”፤ “ግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ የማይናወጥ ነው” በማለት ዋና ዳይሬክተሩ አበክረው ይገልፃሉ። አርሶ አደሮች በየጊዜው ቴክኖሎጂ እንደሚፈልጉ፤ ቴክኖሎጂው ደግሞ መነሻውም መዳረሻውም ምርምር ሲሆን ምርምርም ኢንቨስትመንት እና የግብርና ምሁራንን መፈለጉን ገልፀው በህብረት እና በትጋት በመስራት አገር መቀየር እንደሚገባ ምሁራኑን አሳስበው ፕሮግራሙን በይፋ ከፍተዋል፡፡

የሆለታ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ከበደ ስለሽ ማዕከሉ በተለያየ ጊዜ ለሆለታ ከተማ ላደረጋቸው የተሻሻሉ ጊደሮች እና የዲቃላ ከብቶች ስጦታ አመስግነው አሁንም ለወጣቶች እና ለሴቶች ማህበራት በተደረገው የዴይሪ ኮርማዎችን ለማድለብ የተደረገውን ስጦታ ትልቅ ውለታ፣ ትልቅ ስራ እና ትልቅ ተስፋ ለወጣቶቻችን ሰጥታችኋል በማለት በሆለታ ከተማ እና በራሣቸው ስም አመስግነዋል፡፡ አስተዳደራቸውም ከማዕከሉ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡

ብሄራዊ የወተት ከብቶች ምርምር አስተባባሪ ዶ/ር ዘውዴ ወ/አጥር በማዕከሉ የወተት ከብቶችን ምርምር ከታሪካዊ ዳራው ጀምሮ አሁን ላይ እስካለበት ደረጃ ድረስ በፓወር ፖይንት የታገዘ ገለፃ ያቀረቡ ሲሆን የወተት ከብቶች ምርምር እንደ አገር ከመንግስት የሚሰጠውን ስትራቴጂ እና ፖሊሲ ይዞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዝርያን ለማሻሻል እና ለውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም አንድ ሰው በዓመት በአማካይ 2ዐዐ ሊትር ማግኘት ሲገባው በአገራችን አሁን ላይ 7ዐ ሊትር ብቻ ማግኘቱ፤ ስጋም ሌላው ዓለም በዓመት 45 ኪሎ ግራም በዓመት በአማካይ ማግኘት ሲቻል በኢትዮጵያ ግን 9 ኪሎ ግራም ብቻ መገኘቱ ቁጭት እንደሚጭር ገልፀው ዛሬ የሚከናወነው ፕሮግራም የወንድ ጥጆችን የማድለብ ቴክኖሎጂ ከነሙሉ ፖኬጁ በማህበር ለተደራጁ አርሶ አደሮች በማስተላለፍ የማድለቡን ተግባር ማስጀመር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በማዕከሉ በምርምር ጥናት የወጣው የማድለብ ቴክኖሎጂ አሁን ላይ 96 የተሻሻሉ ኮርማዎችን ለአርሶ አደሮች ሲያስተላልፍ በዋጋ ተመን ረገድ ከ25ዐ,0ዐ0 ብር ጀምሮ እስከ 4ዐዐ,ዐ00 ብር ድረስ ሊሸጡ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ይኸውም ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ከተጠቃሚዎች እና ከተሣታፊዎች ምስጋና የቀረበ ሲሆን እንደ አስተያየት ወንድ ጥጆች ሲወለዱ አማራጭ የሆነ የማድለብ ቴክኖሎጂ በምርምር እና በጥናት መታገዙ እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከሌማት ትሩፋት ጋር የተቀናጀ ሥራ መሠራቱ አዋጭ እንደሚያደርገው በተሣታፊዎች ተገልጿል፡፡ በእርግጥም ከዚህ በፊት ዲቃላ ኮርማዎች ለምግብነት የማይፈለጉ ሲሆን አሁን ላይ ባላቸው የስጋ ብዛት እና መጠንን ጨምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንደመጣ በውይይት ተነስቷል፡፡ በመጨረሻም ዶ/ር ፈቃደ ፈይሣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የመዝጊያ ንግግር አድርገው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply