የብሔራዊ ጥጥ ምርምር የመስክ ቀን አካሄደ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት/ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም.

የጥጥ ምርምር በተቋሙ በወረር ምርምር ማዕከል በዋናነት የተሻሻሉ የጥጥ ዝርያዎችን ማውጣት ይቻል ዘንድ ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ተቋቋመ። በቆይታውም በሽታና ተባይን መቋቋም የሚችሉ 43 ዝርያዎችን በማውጣት ጥጥ ላይ ለተሠማሩ አርሶ/አርብቶ አደሮች፣ የግል ባለሀብቶች እንዲሁም በሰፋፊ የጥጥ እርሻ ላይ ለተሠማሩ ባለሀብቶች በአገሪቱ ብቸኛ ዘር አቅራቢ ሆኖ ጉልህ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የወረር ምርምር ማዕከል ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በመልካ ሰዲ ብሔራዊ የጥጥ ምርምር የመስክ ቀን ያካሄደ ሲሆን በምርምር ማዕከሉ ደግሞ የዘር ብዜት ምርምርን አስጎብኝቷል።

አቶ ሽመልስ አለማየሁ የወረር ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ስለ ጥጥ ምርምር ስኬቶች፣ ተግዳሮቶቾ፣ እና የወደፊት ተስፋዎች በስፋት አብራርተዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለፃ ጥጥ በማዕከሉ ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ በመስኖ በመጠቀም የምርምር ሙከራዎችን በማድረግ የመነሻ ዘር በማውጣት እየሠራ እንደሆን ገልፀዋል። ጥጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሠራ ለአገራችን ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የምናስገባውን መተካት እንደሚቻል አቶ ሽመልስ አበክረው ገልፀዋል።

ዶ/ር በድሩ በሽር በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የም/ም/ዋና ዳይሬክተር ተወካይ የመስክ ቀኑን በይፋ የከፈቱ ሲሆን ተቋሙ ከተቀመጠለት ዓላማ ማለትም ቴክኖሎጂን ከማመንጨት፣ ከማስተዋወቅና ከማሰራጨት አንፃር ማዕከሉ በጥጥ ምርምር የበኩሉን እየተወጣ የሚገኝ ብቸኛ ማዕከል መሆኑን ገልፀዋል።

ለመስክ ምልከታ የቀረበው የመልካ ሰዲ የጥጥ ምርምር የሙከራ ማሣ በ2.5 ሄክታር ላይ የሚደረግ ሙከራ ሲሆን በባዮቴክኖሎጂ የታገዘው እና በሌሎች ዓለማት ውጤታማ በመሆኑ የተመሠከረለት የBT-Cotton ዘር እና በማዕከሉ በምርምር ላይ የሚገኘው የConventional variety ሙከራን በመስክ ላይ ለጉብኝት ቀርቧል። ይሄውም BT-Cotton ለበሽታ እና ለጥጥ ተባይ እስከ 5 ጊዜ በተደጋጋሚ የሚረጨውን የኬሚካል ርጭት የማይፈልግ ሲሆን የConventional variety በጭረት ርዝመት እና በጥራት የተሻለ ቢሆንም የጥጥ ተባይን ለመከላከል በተደጋጋሚ የሚደረገው የኬሚካል ርጭት የሰው ኃይል እና የኬሚካል ዋጋ ከፍተኛ ወጭ መሆኑን የዘርፋ ተመራማሪ አቶ ዶኒስ ጉርሜሳ በግልፅ አስቀምጠዋል።

ተመራማሪ ዶኒስ ጥጥ በከፍተኛ ሁኔታ በAfrican Bollworm እንዲሁም በሌሎች የጥጥ ተባይ የሚጠቃ ሰብል በመሆኑ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚፈልግ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል። ከጥጥ መስክ ጉብኝት በኋላ በቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

+3

All reactions:

121Neba Neba, Take Ethiopiawe and 119 others

Leave a Reply