የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት/ጉራጌ ዞን
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወልቂጤ ምርምር ማዕከል ህዳር 3 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም. በምርምር እና በአርሶ አደር ማሣ የተሠሩ የዘር ብዜት ሥራ፣ የኩታ ገጠም እርሻና፣ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም የተሠሩ ሥራዎችን በአርሶ አደሮች የመስክ ቀን አስጎብኝቷል፡፡
ፕሮግራሙን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት አቶ ቤተል ነክር የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሲሆኑ በንግግራቸው ማዕከሉ በ2ዐ16/17 የምርት ዘመን ከ15ዐ በላይ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ያከናወነ ሲሆን 154 ሄ/ር በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት መታከሙን፤ 24ዐ ሄ/ር በኩታ ገጠም የዘር እርሻ መታረሱን፣ እንዲሁም ስንዴ እና ሽምብራን ጨምሮ በድምሩ 49ዐ ሄ/ር በኩታ ገጠም እርሻ መታረሱን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም አቶ ቤተል ማዕከሉ በቨርሚኮምፖስት የአፈር ማዳበሪያ ፍተሻ፣ አዳዲስ የሰብል ዝርያ፣ ዶሮ፣ የተሻሻሉ የወተት ከብት ጊደር፣ የተሻሻለ መኖ፣ የተፋሰስ የአፈርና ውኃ እቀባ፣ የድንች ዝርያ ማደስ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ማነቆዎችን ለይቶ ውጤታማ ስራ እንዳከናወነ ገልፀዋል፡፡
አቶ ቤተል በመጨረሻም ለሥራቸው ደጋፊ እና ተባባሪ የነበሩትን EIAR-CALM and FSRP የተባሉ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ለጉራጌ ዞን አስተዳድር እና የወረዳ ኃላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር መኩሪያ ታደሰ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ እንደገለፁት የወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል ከተመሠረተ አነስተኛ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም በጉራጌ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች እያከናወነ የሚገኘው የምርምር ሂደት እጅግ የተሣካ፣ ውጤታማ እና አኩሪ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ ዶ/ር መኩሪያ ገለፃ ማዕከሉ በሰው ኃይል ቁጥር ከሌሎች ማዕከላት ያነሰ ቢሆንም ይኼንን ያህል ተግባር ማከናወኑን በአድናቆት ገልፀዋል
ዶ/ር ገረመው ታየ በተቋሙ የማዕከላት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በጉራጌ ዞን በሶስቱም ወረዳዎች የተሠሩት የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ስራ እጅግ የተዋጣለት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎችም ሆኑ የማዕከል ዳይሬክተሩ ሊመሠገኑ እንደሚገባ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ በመስክ ቀኑ የቀረቡ በዞኑ በጌታ ወረዳ በተጎዳ እና በተራቆተ መሬት ላይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም 5ዐ ሄ/ር የገብስ ክላስተር፤ በጉመር ወረዳ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም የተሠራ ሥራ፤ በጆምቦሮ የምርምር ጣቢያ የተከናወነ የገብስ፣ የስንዴ እና የድንች የዘር ብዜት ሥራዎች ሲሆኑ በመስክ ቀኑ ሁሉም ተጎብኝተዋል፡፡
በዕለቱ የዋናው መ/ቤት እና የጉራጌ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ኃላፊዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ አርሶ አደሮች እና የማዕከሉ ተመራማሪዎች ታዳሚ ሆነዋል፡፡በመጨረሻም ሙያዊ ውይይት ተደርጓል፡፡
፡

