You are currently viewing የሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከልበተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ዙሪያ የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን አካሄደ

የሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከልበተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ዙሪያ የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን አካሄደ

  • Post author:
  • Post category:News
  • Post comments:0 Comments
  • Reading time:1 mins read

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
ጥቅምት 3ዐ ቀን 2ዐ17 ዓ.ም. /ሆለታ/

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ምርምር ማዕከል ጥቅምት 3ዐ ቀን 2ዐ17 ዓ.ም. የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን ፕሮግራም አካሄደ፡፡ ፕሮግራሙን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈተቱት ዶ/ር ገመቹ ቀነኒ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሲሆኑ አጠቃላይ የማዕከሉን እንቅስቃሴ ለተሣታፊዎች አቅርበዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ገመቹ ገለፃ ማዕከሉ ከተመሰረተ 6ዐ ዓመታትን ያስቆጠረና አንጋፋ ማዕከል ሲሆን የሰብል፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የእንስሳት ምርምር ዘርፍም አብሮ ተመስርቷል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ገመቹ ጨምረውም የማዕከሉ የእንስሳት መኖና ስነ-ምግብ ምርምር ከተባባሪ አካላት ጋር በተለይም ደግሞ ከዓለም ዓቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም /ILRI/ ጋር በቅንጅት ባደረጉት የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ሰብሎች ምርምር ላይ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ እና የቅደመ-ማስፋፋት ስራዎች በኤጀሬ፣ በወልመራ እና ገፈርሳ ጉጂ ወረዳዎች በአርሶ አደር ማሣ ላይ ተሞክረው ለጉብኝት ቀርበዋል ብለዋል፡፡

ዶ/ር መስፍን ደጀኔ በማዕከሉ የእንሰሳት መኖና ስነ-ምግብ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የእንስሳት ምርታማነትን ከሚገዱቡት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የእንስሳት መኖ እጥረት መሆኑን ገልፀው የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ሰብሎችን ማለትም እንደ ናፒር ሣር ያሉትን የሣር መኖዎች ከሌሎች ሰብሎች ጋር በማቀናጅት በተለይም የወተት ላሞችን ምርታማነት መጨመር እንደሚቻል የምርምሩን ውጤት እንዲሁም በአርሶ አደር ማሣ የተደረገውን ሙከራ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር መስፍን በበጋ ማለትም የግጦሽ ሳርና የእህል ተረፈ-ምርት በብዛት በማይገኝበትና የእንስሳት የሥነ-ምግብ ጥራት አስቸጋሪ በሚሆንበት ወቅት በእንስሳት ምርታማነት ላይ የሚታየው ውጤት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በቂ ባልሆነ አመጋገብ የአንስሳት እድገት እና የወተት ምርት መቀነስ የአርሶ አደሩንም ገቢ በእጅጉ እየቀነስ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በምርምር መቅረፍ ይቻል ዘንድ በማዕከሉ አስተባባሪነት ሥነ-ምህዳርን ያማከለ በሆለታ፣ ደብረ ዘይት እና ወንዶ ገነት ዝርያን ለመምረጥ የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ ይገኛል በማለት ገልፀዋል፡፡ በማዕከሉ የእንስሳት ምርምር ግቢ በብዜት ላይ የሚገኙ የናፒር ሣር የመነሻ ዘር ብዜት ሥራዎች፣ በኤጀሬ፣ ወልመራና ገፈርሳ ጉጂ በአርሶ አደር ማሣ ላይ የተደረጉ ተስፋ ሰጭ ሥራዎች ለመስክ ምልከታው መቅረባቸውን አብራርተዋል፡፡

የተሰሩ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ሰብሎችን የማስተዋወቅ፣ ስራዎችንም የመገምገም ሂደት በአርሶ አደሮች ማሣ ተከናውኗል፡፡ ይኸውም አርሶ አደር አበራ ጫሊ፣ ዓለሙ አሸናፊ፣ ደጀኔ ለሜሣ እና ሴት አርሶ አደር ሽዋየ ዓለሙ እንደገለፁት ቴክኖሎጂው ሁሉም ሰው ሊተገብረው የሚችል ሲሆን በጓሮ አትክልት መልክ እየተሠራ በየሁለት ወሩ በማጨድና ከሌሎች ሰብሎች ጋር በማቀናጀት ለወተት ላሞች በማቅረብ ምርት መጨመር እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ በምርምሩ ድጋፍ የቀረበላቸው የቴክኖሎጂ ፓኬጅ ከፍተኛ ወጭ ያስወጣቸው የነበረውን የፋጉሎ ችግር እንደቀረፈላቸውም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ሙያዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ዶ/ር ፈቀደ ፈይሣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር የመዝጊያ ንግግር አድርገው የመስክ ቀኑ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply